ኢሳት (ነሃሴ 9 ፥ 2008)
ላለፉት ሁለት ሳምንታት ህዝባዊ ተቃውሞን ሲያካሄዱ የቆዩ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች እሁድ የጀመሩትን ከቤት ያለመውጣት አድማ ሰኞ ለሁለተኛ ቀን መቀጠላቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ሰኞ ለኢሳት አስታወቁ።
የከተማዋ ነዋሪዎች የጀመሩትን ይህንኑ ከቤት ያለመውጣት አዲስ አድማ ተከትሎ በከተማዋ የሚገኙ የመንግስትና የግል አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሙሉ ለሙሉ ስራ ማቆማቸው ታውቋል።
የከተማዋ አስተዳደር ባለስልጣናት ነዋሪዎች የተለመደ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸውን እንዲቀጥሉ በድምፅ ማጉያ ቅስቀሳን ቢያደርጉም በተቃውሞ የሰነበቱ ነዋሪዎች ምላሽ አለመስጠጣታቸውን ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል።
ከተማዋ የተወረረች እንደምትመስል የተናገሩት እማኞች ህዝቡ ራሱን በማስተባበር አዲስ የተቃውሞ ስልፍ መጀመሩን አክለው ገልጸዋል።
ከቤት ባለመዉጣት አድማ ላይ የሚገኙ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በእለት ተዕለት የተለያዩ ስራዎች ራሳቸውን የሚያስተዳድሩ ሰዎች እንዳይጎዱ በማሰብ ድጋፍ እየሰጡ መሆኑን በዚሁ ድርጊት የተሳተፉ አንዲት ሴት ለኢሳት አስታውቀዋል።
ላለፉት ሁለት ሳምንታት በጎንደርና ባህርዳር ከተሞች እንዲሁም በዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች ህዝባዊ ተቃውሞዎች ሲካሄዱ የሰነበቱ ሲሆን፣ በባህርዳር ከተማ ብቻ 55 ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸው ይታወሳል።
ይህንኑ ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የክልሉና የፌዴራል ባለስልጣናት የሃይማኖት አባቶች በማስተባበር ተቃውሞ እንዲረግብ የማግባባት ስራን ሲያካሄዱ እንደቆዩ በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች ለኢሳት አስረድተዋል።
ለሁለተኛ ቀን ሰኞ ቀጥሎ ያለው ከቤት ያለመውጣት ተቃውሞ ህዝቡ ያለውን ቁጣ በሰላማዊ መንገድ ለመግለጽ የወሰደው እርምጃ መሆኑን የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ገልጸዋል።
በጎንደር ከተማ ያሉ የመግንስት የጸጥታ ሃይሎች በገዛ ወገኖቻቸው ላይ መተኮስን ትተው የህዝቡን ቅሬታ በአግባቡ እንዲረዱ እጠይቃለሁ ሲሉ አንዲት አዛውንት ለኢሳት ተግረዋል።
የኢትዮጵያ ህዝቡም በዘርና በሃይማኖር ሳይከፋፈል ትግሉን መቀጠል እንዳለበትና የጸጥታ ሃይሎችም ከህዝቡ ጎን መቆም እንደሚገባቸው እኚሁ አዛውንት ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ጠይቀዋል።