ኢሳት (ነሃሴ 12 ፥ 2008)
በተለያዩ የተቃውሞ ስልቶች ውስጥ የቆዩ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች ከፊታችን ቅዳሜ ነሃሴ 14, 2008 ዓም ጀምሮ “ነጭ በመልበስ” እና በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተገደሉ ሰዎችን ለማሰብ አዲስ መርሃግብር መንደፋቸውን ሃሙስ አስታወቁ።
ጥቁር በመልበስና ከቤት ባለመውጣት አድማ ውስጥ የቆዩት ነዋሪዎቹ ሙሉ በሙሉ ነጭ የመልበሱ ስነ-ስርዓት የቀድሞ ጠቃላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን የመታሰቢያ ዝጅግት በሚያካሄዱበት ቀን በተቀራኒ አለባበስ ተቃውሞን ለማንጸባረቅ እንደሆነ አስረድተዋል።
የጀመሩት ተቃውሞ በተለያዩ መልኮች ቀጣይ እንደሚሆን የተናገሩት ነዋሪዎች የከተማ ህዝብ ከቅዳሜ ጀምሮ ሁለት መልዕክቶችን ማስተላለፍ እንደሚጀምር ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።
በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተገደሉ ሰዎች ብሩህ ተስፋችን ነው ሲሉ የገለጹት የጎንደር ከተማን ነዋሪዎች፣ ቅዳሜ የሚጀምረው ነጭ የመልበስ ስነስርዓቱ ታስቦበት የተዘጋጀ መሆኑን አክለው ገልጸዋል።
ከሳምንት በፊት የከተማዋ ነዋሪ የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ ጥያቄን ማቅረብ በጀመሩ ጊዜ የጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት የሃይል ዕርምጃ ባህር ዳር ከተማን ጨምሮ ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።
በጸጥታ ሃሎች የተወሰደው ይህንኑ ድርጊት በመቃወም የአካባቢው ነዋሪ ተቃውሞን በተለያዩ መንገድ በመግለጽ ላይ ሲሆን፣ የጎንደር ከተማ ህዝብ ከሶስት ቀናቶች ከቤት ያለመውጣት አድማ ሲያካሄድ ቆይቷል።
የፊታችን ቅዳሜ የሚካሄደው ነጭ የመልበስ ስነስርዓት የዚሁ ተቃውሞ አካል መሆኑንና ነዋሪዎች ራሳቸውን በማስተባበር የተለያዩ ስልቶችን ለመጠቀም መግባባትን እያደረጉ እንደሆነ ከሃገር ቤት የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች በተመሳሳይ መልኩ ለሁለት ቀን የስራ ማቆም አድማ ሲያደርጉ መቆየታቸውም የሚታወስ ነው።
በርካታ የፌዴራልና የክልሉ ልዩ ሃይሎች አሁንም ድረስ በዋና ዋና ከተሞች ሰፍረው እንደሚገኙና የማህበራዊ የኑሮ እንቅስቃሴዎች እንደወትሮው በመከናወን ላይ አለመሆኑን እማኞች ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።
ከሳምንት በፊት በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የተነሱ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን ለመቆጣጠር ሲሉ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት እርምጃ ከ100 በላይ ሰዎች የተገደሉ መሆናቸውን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።