ኢትዮጵያ በቢጫ ወባ በሽታ ስርጭት ሰለባ ልትሆን እንደምትችል ተነገረ

ኢሳት (ነሃሴ 12 ፥ 2008)

ኢትዮጵያን ጨምሮ የወባ በሽታ ተጋላጭ የሆኑ የአፍሪካ ሃገራት በአንጎላና ዴሞክራቲክ ሪፕሊክ ኮንጎ እየተስፋፋ ባለው የቢጫ ወባ በሽታ ስርጭት ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉ የአለም ጤና ድርጅት ረቡዕ አሳሰበ።

ካለፈው ወር ጀምሮ በሁለቱ ሃገራት ከ400 በላይ ሰዎች በበሽታው ስርጭት የሞቱ ሲሆን፣ ከስድስት ሺ የሚበልጡ ተጨማሪ ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን ሲ ኤን ኤን የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።

በወባ ትንኝ አማካኝነት የሚተላለፈው የቢጫ ወባ በሽታ ታማሚዎችን በአጭር ጊዜ ለህልፈተ ህይወት የሚዳርግ ሲሆን፣ ከፍተኛ የወባ ተጋላጭ የሆኑ ከ10 በላይ የአፍሪካ ሃገራት ለቢጫ ወባ በሽታው ተጋላጭ ይሆናሉ ተብሎ ተሰግቷል።

ኢትዮጵያ ካላት ከ90 ሚሊዮን ህዝብ መካከል ከ40 ሚሊዮን የሚበልጡት ለወባ በሽታ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች እንደሚኖሩና በርካታ ሰዎች በየአመቱ እንደሚሞቱ የአለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

በአንጎላና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በመሰራጨት ላይ ያለውን የቢጫ ወባ በሽታ ተከትሎ የአለም ጤና ድርጅት በሽታውን ለመቆጣጠር ርብርብ እያደረግ የሚገኝ ሲሆን፣ በሽታውን ለማከም የሚረዳ መድሃኒት እጥረት መኖር ችግሩን ያባብሰዋል ተብሎ ስጋት መኖሩን አመልክቷል።

ለአፍሪካ ከፍተኛ ስጋት ሆኗል የተባለው ይኸው ወረርሽን በቀጣዮቹ ወራት አውሮፓ እና አሜሪካ ሊዛመት እንደሚችል የጤና ድርጅቱ አክሎ መግለጹን ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ዘግቧል።

በመዛመት ላይ ላለው የቢጫ ወባ በሽታ መከላከያ የሚያስፈልገውን መድሃኒት ለማምረት በትንሹ ስድስት ወር የሚፈጅ ሲሆን፣ የመድሃኒቱ አቅርቦት አለመኖር የበሽታውን ስርጭት ሊያፋጥነው ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።

የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ የዚካ ቫይረስን ጨምሮ በወባ ትንኝ አማካኝነት የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመቆጣጠር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ረቡዕ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሞዛምቢክ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ፣ ጊኒ ቶጎ እና ጎረቤት ሱዳን በአፍሪካ የወባ ተጋላጭ ከሆኑ ሃገራት መካከል ዋነኞቹ ሲሆኑ በአህጉሪቱ በየአመቱ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ሰው በወባ በሽታ እንደሚሞት መረጃዎች ያመለክታሉ።