ጥር ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡት የግብጹ መሪ ሙሀመድ ሙርሲ በወታደሮችና በተቃዋሚዎች ድጋፍ ከስልጣን ከተወገዱ በሁዋላ የሽግግር መንግስቱ አዲስ ህገመንግስት በማርቀቅ ድምጽ እንዲሰጥበት አድርጓል።
ባለፉት ሁለት ቀናት በተሰጠው ድምጽ አብዛኛው ህዝብ አዲሱን ህገመንግስት ይደግፋል ተብሎ ይጠበቃል።
በአዲሱ ህገመንግስት አንድ ፕሬዚዳንት ለ2 ጊዜ ብቻ የሚመረጥ ሲሆን ፓርላማውም ፕሬዚዳንቱን ከስልጣን የማንሳት መብት ተሰጥቶታል። ህገመንግስቱ እስልምና የአገሪቱ ብሄራዊ ሃይማኖት ቢሆንም፣ ሌሎች ሀይማኖቶችም በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ ይፈቅዳል። በዘር፣ በጾታ፣ በአካባቢና በሀይማኖት ላይ ተንተርሶ የፖለቲካ ድርጅት ማቋቋም በአዲሱ ህገመንግስት አይፈቀድም። አንዳንድ ተችዎች በህገመንግስቱ” ለሚቀጥሉት 8 አመታት የመከላከያ ሚኒስትሩን የሚሾመው ጦሩ በመሆኑ ስልጣኑ በጦሩ እጅ ሊቆይ ይችላል” ይላሉ።
የሙርሲን መንግስት በማውረድ ከፍተኛ ሚና ተጫወቱት ጄኔራል አብደል አል ፋታህ አል ሲሲ ለፕሬዚዳንትነት ሊወዳደሩ እንደሚችሉ እየተነገረ ነው።
ግብጽ በህዝባዊ ተቃውሞ የሆሲኒ ሙባረክን መንግስት ካፈራረሰች በሁዋላ፣ ብዙዎች እንደተመኙት በመልካም የዲሞክራሲ ጎዳና ላይ አትገኝም።