በደቡብ ሱዳን የሚካሄደው አስከፊ ጦርነት እንደቀጠለ ነው

ጥር ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሁለቱም ተፋላሚ ሃይሎች በአዲስ አበባ የሰላም ድርድር እያደረጉ ቢሆንም፣ ጦርነቱ ግን በመሬት ላይ እየተካሄደ መሆኑን የሚወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ። ከቀናት በፊት በነዳጅ ሀብቱ የበለጸገው አፐር-ናይል ስቴት የተበላውን ግዛት ዋና ከተማ ማላካልን መቆጣጠራቸውን  የመንግስት ሃይሎች ቢያስታውቁም፣ የአማጽያኑ መሪ የሆኑት ሪክ ማቻር ከተማዋን መልሰው መቆጣጠራቸውን አስታውቀዋል።

የአማጽያኑ የድል ወሬ እንደተሰማ መንግስት ጦርነት የተካሄደ በሆንም፣ ከተማዋ ግን አሁንም በመንግስት ጦር ቁጥጥር  ስር መሆኑዋን በመግለጽ የተቃዋሚዎችን ዜና አጣጥሎአል።

የሰለም ስምምነቱ እንዲሰምር የተለያዩ ሃያላን መንግስታት ግፊት ቢያደርጉም እስካሁን ድረስ ይህ ነው የሚባል ውጤት አልተገኘም። አማጽያኑ የታሰሩ ባልደረቦቻቸው እንዲፈቱ እየጠቁ ሲሆን፣ መንግስት ግን ሰዎችን መፍታት የማይታሰብ ነው ይላል። አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት አገራት ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር እስረኞችን እንዲፈቱ ግፊት በማድረግ ላይ ናቸው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኡጋንዳ ጦሩዋን በይፋ ወደ ደቡብ ሱዳን እንድትል ፓርላማው ፈቃድ ሰጥቷል። ፓርላማው ውሳኔ ላይ የደረሰው የጸጥታው ምክር ቤት ማንኛውም አገር ጦሩን ወደ ደቡብ ሱዳን እንዳይልክ ባሳሰበበት ወቅት ነው። የኡጋንዳን መንግስት ጦሩን የምልከው በአገሪቱ ያሉ ዜጎቼን ለመንከባከብ ነው ቢልም፣ የተቃዋሚው መሪ ግን ” ኡጋንዳ በሌላ ሰው አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገባች ነው” በማለት ተቃውመዋል።

በነዳጅ ሀብቷ የበለጸገችውን አገር ለመቆጣጠር በሚደረገው ጣልቃ ገብነት ምስራቅ አፍሪካ በጦርነት ሊታመስ ይችላል የሚሉ ስጋቶች እየቀረቡ ነው።