የግል ድርጅቶች ሠራተኞች አዲስ የተረቀቀውንና የፕሮቪደንት ፈንድ የሚያሳጣቸውን ሕግ በመቃወም ገንዘባቸውን እያወጡ ነው።

ግንቦት ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የግል ድርጅት ሠራተኞች የጡረታ አዋጅን በማሻሻል ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ፕሮቪደንት ፈንድ ሲያጠራቅሙ የቆዩ የግል ሠራተኞችን በጡረታ እንዲታቀፉ በማድረግ ሰበብ
ፕሮቪደንት ፈንዳቸውን ለመውረስ የሚያስችል ሕግ ሰሞኑን ለፓርላማ መቅረቡ ከተሰማ ወዲህ በርካታ ሠራተኞች ከአሰሪዎቻቸው ጋር በመነጋገር ገንዘባቸውን ሕጉ ከመተግበሩ በፊት እያወጡ መሆኑን ዘጋቢያችን ገልጿል፡፡
ፓርላማው የቀረበለት የግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 715/2003 ማሻሻያ ከመውጣቱ በፊት በተቋቋሙ የግል ድርጅቶች የፕሮቪደንት ፈንድ ሽፋን ያላቸው ሠራተኞች በነበራቸው የፕሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚነታቸው ለመቀጠል
ከወስኑ ወይም በግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ ዐቅድ ስለሚሸፈኑበት ሁኔታ ሊስማሙ እንደሚችሉ በደነገገው መሰረት በተለይ እንደባንክና ኢንሹራንስ ያሉ ትልልቅ የንግድ ኩባንያዎች በፕሮቪደንት ፈንድ መርጠው ሠራተኞቻቸውን ተጠቃሚ
አድርገዋል፡፡
ይሁን እንጂ ዜጎችን በአንድ የማህበራዊ ዋስትና ዐቅድ ሥርዓት ውስጥ ተጠቃሚ ማድረጉ በዜጎች መካከል የሚኖረውን የመብትና የጥቅም ልዩነት የሚያስወግድ ከመሆኑም በላይ ችግርንና ጥቅምን የመጋራት መርህን የሚከተል በመሆኑ እንዲሁም
ሠራተኛው የፕሮቪደንት ፈንድ ተጠቃሚነት የመቀጠል ውሳኔ የሠራተኛውን ተተኪዎች የዘለቄታ ማህበራዊ ዋስትና መብትና ጥቅም የሚያሳጣ በመሆኑ ከሰኔ 16 ቀን 2003 ዓ.ም በፊት ተቀጥረው ይሰሩ በነበሩበት የግል ድርጅት ውስጥ
የፕሮቪደንት ፈንድ የነበራቸውና በዚሁ የቀጠሉ ሠራተኞች በግል ድርጅቶች ሠራተኞች ጡረታ ዐቅድ እንዲሸፈኑ መታቀዱ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ተደንግጓል፡፡
በዚህ ድንጋጌ መሰረት የግል ድርጅቶች ሠራተኞች የፕሮቪደንት ፈንድ ወደ ግል ድርጅቶች ሠራተኞች ጡረታ ፈንድ እንደሚዛወር ወይም ገንዘቡን መንግሰት እንደሚወስደው ያስቀምጣል፡፡ ሆኖም ሕጉ ወደኃላ ሄዶ የሠራተኞችን የፕሮቪደንት
ፈንድ ለመውሰድ መቋመጡ በርካታ የግል ሠራተኞችን አስቆጥቶአል፡፡
አንድ በባንክ ሙያ ውስጥ የተሰማራ ባለሙያ ለዘጋቢያችን እንደተናገረው መንግስት በየጊዜው በሚለዋውጠው ህግ የራሱን ጥቅም ብቻ አስቀድሞ የሚያይ መሆኑ እንደሚያሳዝነው ጠቁሞ፣ ራሳችን ያጠራቀምነውን ፕሮቪደንት ፈንድ በመውሰድ
በጡረታ ተጠቃለሉ ማለቱ ብዙ ሠራተኞችን አስቆጥቷል ብለዋል፡፡ ስለሆነም ሁሉም ሠራተኛ ገንዘቡን መውሰድ በሚችልበት ሁኔታ ላይ እየመከረ ነው ብለዋል፡፡
ፕሮቪደንት ፈንድ ማለት ከሠራተኛውና ከአሠሪው በየወሩ የተወሰነ መቶኛ እየተዋጣ በሠራተኛው ስም የሚቀመጥና ሠራተኛው በጡረታ ጊዜ ወይንም በሥራ በማናቸውም ምክንያት ሲለቅ ተጠራቅሞ የሚወስደው ገንዘብ ነው።