በአማራ ክልል የጀልባ አገልግሎት ሰጪ ነጋዴዎች ለረዢም ጊዜ በመታገዳቸው ችግር ላይ መሆናቸውን ተናገሩ

ግንቦት ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በጣና ሃይቅ ላይ በቱሪስት ጀልባ ትራንስፖርት የሚያገለግሉ የጀልባ ባለሃብቶችና ካፒቴኖች፣ “የአማራ ክልል ንግድና ትራንስፖርት ቢሮ ‘ህገ ወጥ’ ናችሁ በሚል ያለፍርድ ቤት
ትዕዛዝ አስራ ሰባት ጀልባዎችን ከሶስት ወር በላይ በማሰሩ ቤተሰቦቻቸውንና ራሳቸውን ለማስተዳደር መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡
ሶስት መቶ ያህል ቤተሰብ የሚያስተዳድሩት ቅሬታ አቅራቢዎች ፣ ለአመታት በስራው ላይ ሲቆዩ በደንበኞች ዘንድ ታማኝነትን ከማትረፋቸውም በላይ ከተለያዩ የአለም ሀገራት ለጉብኝት ከሚመጡ የውጭ ዜጎች ጋር በፈጠሩት መልካም ግንኙነት
የገዢው መንግስት ካድሬዎችና የከፍተኛ አመራር ጀልባዎች ገበያ በማጣታቸው ምክንያት ጀልባቸውን እንዳይሰሩባቸው ማገዳቸውን ተናግረዋል፡፡
በአማራ ብሔራዊ ክልል መንግስት ምክር ቤት ባወጣው የጉብኝት እና መስተንግዶ ሥርዓት መወሰኛ ደንብ ቁጥር80/2003 እንደሚገልጸው ‹‹ የቱሪስት አጓጓዥ ማለት በመደበኛው የህዝብ ትራንስፖርት ስምሪት ውስጥ ሳይገባ ለቱሪስቶች
በአየር፣ በየብስም ሆነ በባህር የማጓጓዝ አገልግሎት የሚሰጥ ግለሰብ ወይም ድርጅት ነው፡፡ ›› ቢልም የትራንስፖርት ቢሮው ‘ስምሪት ውስጥ ገብታችሁ በተራ ልትሰሩ ግድ ነው’ በማለት የውጭና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ባልፈለጉትና
ባልመረጡት ጀልባ እንዲስተናገድ እያስገደዱት መሆኑ የጀልባ ማህበሩ አመራሮች ገልጸዋል፡፡
ቢሮው ስራቸውን በቅርበት ተከታትሎ እንደማያውቅ የሚገልጹት ቅሬታ አቅራቢዎች የቢሮው ባለሙያዎች በኩንትራት ጀልባዎች አሰራር ዙሪያ ያላቸው እውቀት ዝቅተኛ በመሆኑ ስራውን በበላይነት እንዲቆጣጠር ሃላፊነቱን የሰጡት እንደ ሌሎቸ በትራንስፖርት አገልግሎት ለተሰማራው ተፎካካሪ የጣና ሃይቅ ትራንስፖርት ድርጅት መሆኑ በስራቸው ላይ በየጊዜው እንቅፋት እንዲፈጠር ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ወጣቶቹ በመጨረሻም ጉደዩን በህግ በማቅረብ እንዲታይ ቢያደርጉም ትርጉም ያለው ውሳኔ ሳያገኙ ወራቶች በመቆጠራቸው ከነቤተሰቦቻቸው ችግር ላይ መውደቃቸውን ገልጸው፤አእምሮአችን እያወቀ ለግለሰቦች ጥቅም ሲባል ያለ ደንብና
መመሪያው ከምንሰራ ጀልባዎቻችን በመሸጥ ለመሰደድ እንደሚገደዱ በምሬት ተናግረዋል፡፡