ሰኔ ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና :-የአዲስ አበባ የቤቶች ልማት የቁጠባ ፕሮግራም መንግስታዊ በሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ እንዲከናወን መደረጉ በግል ባንኮች ላይ ከፍተኛ ኪሣራ እያስከተለ እንደሆነና በአጭር ጊዜ የግል ባንክ ዘርፉን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል አዲስ አድማስ ዘገበ፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የግል ባንክ ባለሙያ፤ እሣቸው በሚሠሩበት ባንክ ደንበኛ የነበሩ ግለሠቦች በቤቶች የቁጠባ ፕሮግራም ተሣታፊ ለመሆን ከባንኩ ገንዘብ በማውጣት በመንግስት ባንኮች እያስቀመጡ መሆናቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።
የባንክ ሂሣብ ለመክፈት ወደ ባንካችን የመጣ ደንበኛ እንዳላጋጠማቸው የዘገበው ጋዜጣው፣ በባንኩ ያላቸውን ገንዘብ ለማውጣት የሚመጡ ደንበኞች መበራከታቸውንና ይህም ባንኩ ራሱን ለማቋቋም ለዓመታት የደከመበትን ልፋቱ ከንቱ እንደሚያስቀረውና ቀጣይ ህልውናውንም አደጋ ላይ እንደሚጥለው ተዘግቧል።
በአሁን ሠአት የግል ባንኮች የውጭ ምንዛሬ እና የሃዋላ አገልግሎቶችን ከመስጠት ባለፈ አዳዲስ የባንክ ሂሣብ የሚከፍቱ ደንበኞች እያስተናገዱ አይደለም።