በክልል ከተሞች ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ተቃውሞአቸውን አሰሙ

ሰኔ ፳፩ (ሀያ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና :-በአዳማ በአቡበክር መስጊድ በተካሄደው ተቃውሞ ሙስሊም ኢትዮጵያውያኑ ” መንግስት ድምጻችንን ይስማ፣ በሀሰት ክስ አንገዛም፣ አሸባሪዎች አይደለንም” የሚሉና ሌሎችንም መፈክሮች አሰምተዋል። በአሳሳ ከተማም እንዲሁ በአል ከራም መስጂድ ተቃውሞ መካሄዱን ለማወቅ ተችሎአል። በወልድያም እንዲሁ ሙስሊሙ ኢትዮጵያውያን ተቃውሞ አሰምተዋል።

በሁለቱም ቦታዎች የተካሄዱት ተቃውሞዎች በሰላም ተጠናቀዋል። መንግስት የድምጻችን ይሰማ መሪዎችን ከእስር በመፍታት ለሙስሊሞች ጥያቄ መፍትሄ እንዲሰጥ ከፍተኛ ጫና ቢደረግበትም፣ አቋሙን የሚቀይር ሆኖ አልተገኘም። ዘወትር አርብ የሚደረጉ ተቃውሞዎችን መንግስት አሸባሪዎች የሚያቀናብሩት ነው በማለት ተደጋጋሚ መግለጫ ሲሰጥ ቆይቷል።