የጋዝጊብላ ነዋሪዎች ኢህአዴግ ክዶናል ሲሉ ተናገሩ።

ሰኔ ፰(ስምንት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ከትግራይ ህዝብ በመቀጠል ኢህአዴግ ወደ ስልጣን እንዲመጣ ከፍተኛ የህይወት መስዋትነት የከፈለው የሰቆጣና አካባቢዋ ነዋሪዎች ቢሆኑም፣ ኢህአዴግ አዲስ አበባ ከገባ ጀምሮ እንደረሳቸው ገልጸዋል።

ከሶቆጣ 48 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘዋ ጋዝጊብላ ወረዳ የሚኖሩ የቀድሞ ታጋዮች ለኢሳት እንደገለጹት፣ ለኢህአዴግ ልጁን ያልገበረ ሰው ባይኖርም፣ ባለስልጣናቱ ግን ውለታቸውን መርሳታቸውን ተናግረዋል።

ከሰቆጣ ላሊበላ የህዝብ ትራንስፖርት አለመኖሩን ፣ ከአዲስ አበባ ሰቆጣ ደግሞ አገር አቋራጭ አውቶቡሶች ያልተመደቡ መሆናቸውን የሚገልጹት ነዋሪዎች ከአዲስ አበባ ሰቆጣ ለመድረስ ደሴ ከተማ ላይ እስከ 4 ቀናት መጠበቅ ግድ እንደሚላቸው ተናግረዋል። ከ 17 አመታት በፊት የተጀመረው ከአለም ከተማ ወደ ላሊበላ የሚወስደው መንገድም በአየር ላይ መቅረቱን ገልጸዋል። ህዝቡ ተቃውሞ ሲያሰማ ” ዛሬ ነገ ይሰራል” በማለት እንደሚደልሉት የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ መንግስት ለጥያቄያቸው መልስ ከመስጠት ይልቅ ህዝቡን መከፈፋል መምረጡን ገልጸዋል።

አቶ በረከት ስምኦንና ሌሎች ባለስልጣኖች ሲመጡ የህዝቡን ችግር ሰምተው እንዳልሰሙ ሆነው እንደሚያልፉት ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ከዋግ ህዝብ ትምህርት ይውሰድ የሚሉት ነዋሪዎች፣ በተለይ የድሮ ታጋዮች በረንዳ ላይ መውደቃቸውንና የሚሰማቸው ማጣታቸውን ገልጸዋል።