ሐምሌ ፳፯ (ሀያ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በጋዜጠኛ ርእዮት አለሙ ላይ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሶስተኛ ወንጀል ችሎት የሰጠውን የ14 አመት ጽኑ እስራት እና የ33 ሺ ብር የቅጣት ውሳኔ፣ እስካሁን የታሰረችው አንድ አመት ከአንድ ወር ታሳቢ ተደርጎ ወደ 5 አመት ዝቅ እንዲል ወስኗል።
የጋዜጠኛ ርእዮት አለሙ የኢህአዴግ ቀይ እስክርቢቶ የተሰኘ መጽሀፍ ነገ ሀምሌ 28 ቀን 2004 ዓም ከቀኑ 8 ከ 30 ሰአት ላይ በራስ አምባ ሆቴል ይመረቃል።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም እና ዶ/ር ዳኛቸው ወርቁ በዝግጅቱ ላይ ንግግር የሚያደርጉ ሲሆን ፣ የአለማቀፍ ተሸላሚዋ ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል የክብር እንግዳ መሆኑዋን ለማወቅ ተችሎአል። ጋዜጠኛዋ ቀደም ሲል በጋዜጦችና እና በእስር ቤት ውስጥ ሆና የጻፈቻቸው ጽሁፎች ተካተዋል።
ዛሬ ከጠዋቱ 4 ሰአት ላይ ስድስት ኪሎ በሚገኘው ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት ላይ የመሀል ዳኛ ዳኘ መላኩ፣ የቀኝ ዳኛ በላቸው አንሲሾ እና ስማቸው ያልተጠቀሰው የግራ ዳኛ ተገኝተዋል። የመሀል ዳኛው ጋዜጠኛ ርእዮት አለሙ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ከቀረቡባት ሶስት ክሶች ከሁለቱ ነጻ መሆኑዋን እና በአንዱ ክስ ብቻ ጥፋተኛ መሆኑዋን በንባብ አሰምተዋል። የፌደራል አቃቢ ህጉም በአንድ ሰው ላይ ክስ መደራረቡ ወንጀለኛ አያሰኝም ብሎዋል።
በአንደኛው ክስ ማለትም በሽብርተኝነት እና በአሸባሪ ድርጅት ውስጥ በአመራርነት በመሳተፍ በሚለው ክስ ምንም አይነት በአመራርነት የተሳተፈችበት ሁኔታ አልታየም ስለዚህም ተጠያቂ ልትሆን አትችልም ተብሎአል።
የሽብርተኛን ገንዘብ ለጥቅም በማዋል እና በማዘዋወር በወንጀል አንቀጽ 684 በሚለው ክስ ፣ ይህን ሊያስብል የሚችል ሌላ ወንጀል ተሰርቶ የተገኘ ማስረጃ ባለመቅረቡ፣ የገንዘቡ ቁጥርም እጅግ ትንሽ ስለሆነ ፣ በሙያዋ ለሰራቸው ስራ ክፍያ ደሞዝ መሆኑን እና ለዚህም ስራ የተመን ውል እንደነበራቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድታለች ካለ በሁዋላ ነገር ግን በሽብርተኝነት በተፈረጀ ድርጅት ውስጥ በማንኛውም መንገድ መሳተፍ በሚለው የወንጀል አንቀጽ 7 ንኡስ አንቀጽ አንድ ተጠያቂ ትሆናለች ብሎአል።
የኢትዮጵያን ሪቪው ድረገጽ አዘጋጅ ኤልያስ ክፍሌ ሽብርተኛ ተብሎ አልተፈረጀም በሚል ጠበቃው ቢከራከሩም ፣ ኤልያስ ክፍሌ በድረገጹ ፣ ለማን እንደሚሰራ ይታወቃል፣ በውጭ አገር በመንግስት ላይ የሚደረጉ አሉታዊ ስራዎችን እና ፕሮፓጋንዳዎችን ሽፋን ሰጥቶ የሚሰራው ይታወቃል፣ በዚህም ላይ ሌሎች ሰዎችን አደራጅቶ በሌሊት በመርካቶ ተክለሀይማኖት መስቀል አደባባይ ፣ ሀብተጊዮርጊስ ድልድይ ፣ “በቃ” የሚል በመለጠፍ አፍራሽ ሚና ሲጫወት ነበር ብሎአል። የህዝብና የመንግስት ልማቶችን ለማውደም በአዲስ አበባ በደሴ በአዋሳ በነቀምቴ ና በጅማ ሊያደርግ የነበረው ውድመት ተመስክሮበታል፣ ስለዚህ ከእርሱ ጋር መስራት የጋዜጠኝነት ስራ ነው ለማለት አያስደፍርም፣ የጋዜጠኛ አላማም ይህ አይደለም በማለት እስካሁን የታሰረችው ታሳቢ ተደርጎ በ5 አመት እንድተቀጣ ወስኖአል።
የጋዜጠኛ ርእዮት አለሙ ጠበቃ ሞላ ዘገየ እስቲ ደግሞ ወደ ሰበር ሰሚ ፍርድ ቤት የምንሄድበት ሁኔታ ካለም እናጠናዋለን በማለት አስተያየት ሰጥተዋል።
ጋዜጠኛ ርእዮት አለሙ ይቅርታ ለመጠየቅ ፈቃደኛ አለመሆኑ መዘገቡ ይታወሳል።
____________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide