(ኢሳት ዜና–ታህሳስ 4/2010)
የጋምቤላ ክልል ለ10ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአል ከፌደራል መንግስት የተበደረውን የ346 ሚሊየን ብር ብድር በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ ሆኖ መክፈሉ አስታወቀ።
ክልሉ ብድሩን ይክፈል እንጂ አሁንም በክልሉ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን የክልሉ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ጠቁሟል።
ክልሉ ባለፈው መስከረምና ጥቅምት ለመንግስት ሰራተኞች በወቅቱ ደሞዝ መክፈትል አቅቶት በርካታ ችግሮች መፈጠራቸውን ኢሳት በወቅቱ ባቀረበው ዘገባ አመልክቶ ነበር።
የብሔር ብሔረሰቦች ተሳትፎ ለላቀ እድገትና ትራንስፎርሜስን የሚል መሪ ቃል የተቀመጠለት 10ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በአል ሲከበር ዋና አዘጋጅ ሆኖ የተመረጠው የጋምቤላ ክልል ነበር።
ክልሉ በአሉን ድል ባለ ድግስ ከሁለት አመት በፊት ሲያከብር የመደገሻ ገንዘቡን የተበደረው ከፌደራሉ መንግስት ነበር።–346 ሚሊየን ብር ።
የበአሉ ማጌጫ የሆኑትን አልባሳትና ሌሎች ቁሶችን ለክልሉ እንዲያቀርብለት የተመረጠው ደግሞ የሕወሃት ንብረት የሆነው አልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ነበር።
እነዚህ ሁሉ ነገሮችን አሟልቶ አረረም መረረም ድግሴን ተወጣሁት ያለው የጋምቤላ ክልል በአሉን ባከበረ ማግስት ግን የገጠመው ነገር ሌላ ነበር።
ከፌደራል መንግስቱ የተበደረው የ346 ሚሊየን ብር እዳ።
ይህንን እዳ ለመክፈል ተራራ የመግፋት ያህል እንደሆነበት የሚናገረው የክልሉ መንግስት የህንን እዳ ለመክፈል ብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ መግባቱን ነው የክልሉ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ቢሮ ሃላፊው አቶ ላክዴር ላክባር የተናገሩት።
እሳቸው እንደሚሉት እንኳን ከመንግስት አይደልም ከሰውም የወሰድከው ብድር ሰላም አይሰጥህምና ስለዚህ ያለን አማራጭ ሌሎች ችግሮቻችንን ወደ ጎን ትተን እዳችንን ለመክፈል ተገደናል።
ክልሉ ከፌደራል መንግስት ለድግስ በሚል የተበደረውን ገንዘብ ለመክፈል ባደርገው ጥረት ውስጥ በገቢና በወጪው መካከል ክፍተት ተፈጥሮበታል ሲሉ የከተማዋ ከንቲባ መናገራቸውን ባለፈው ሕዳር 21/2010 ኢሳት ባቀረበው ዘገባ ማመልከቱ ይታወሳል።
ይህ ክፍተት ደግሞ ለመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ የመክፈል አቅሙን ክፉኛ እንደተፈታተነውና በወቅቱም መክፈል እንዳልቻለ ዘገባችን ያስታወሳል።
የደሞዝ በሰአቱ ያለመከፈል ችግር ከመንግስት ሰራተኞችና ከመምህራን ዘንድ ከባድ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር።
መምህራንም ችግሩ በውይይት ተፈቷል እስከተባለበት ጊዜ ድረስ ስራቸውን አቁመው እንደነበር ይታወሳል።
በክልሉ ያሉት 1550 ያህል የመንግስት ሰራተኞች የመስከረም ወር ደሞዛቸው የጥቅምት ወር ሊጠናቀቅ ሲል ተሰቷቸዋል።ከነዚህ የመንግስት ሰራተኞች 513ቱ መምህራን ነበሩ።
የጥቅምት ወር ደሞዛቸውም ቢሆን እስከ ሕዳር አጋማሽ ድረስ እንዲጓተት ከተደረገ በኋላ እንዲከፈላቸው ተደርጓል።
አሁን ላይ ክልሉ ያለበትን የፌደራል መንግስት እዳ ከፍሎ ጨርሷል ቢባልም ሌሎች በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ግን የቢሮ ሃላፊው አቶ ላክዴር ላክባር ሳይጠቁሙ አላለፉም።