የሕወሃት መሪዎች የአሜሪካንን ሽምግልናና ድጋፍ ይጠይቁ ተባለ

(ኢሳት ዜና–ታህሳስ 4/2010)

በኢትዮጵያ ሕግና ስርአት ሙሉ በሙሉ ከመፍረሱ በፊት የሕወሃት መሪዎች የአሜሪካንን ሽምግልናና ድጋፍ እንዲጠይቁ አንድ የአሜሪካ የቀድሞ ዲፕሎማት ጥሪ አቀረቡ።

ሀገሪቱን ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ለመውሰድና ሁሉም ፓርቲዎች የሚሳተፉበት ጉባኤ ለማካሄድ የአሜሪካንን አደራዳሪነትና ሽምግልና ሕወሃት እንዲጠይቅ ሀሳብ አቅርበዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር የነበሩት አምባሳደር ኽርማን ኮህን በማህበራዊ ገጻቸው ትላንት ባሰራጩት አጭር መልዕክት የሕወሃት መሪዎች ሁሉ አቀፍ የፓርቲዎች ጉባኤ በሚጠራበት ሁኔታ ላይ የአሜሪካንን ድጋፍ መጠየቅ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ሀገሪቱን ወደ አዲስ ዲሞክራሲያዊ ስርአት የሚወስዳት ይህ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

የሕወሃት መሪዎች ይህንን በማጤን በሀገሪቱ ሙሉ በሙሉ ህግና ስርአት ከመፍረሱ በፊት የአሜሪካንን ድጋፍ መጠየቅ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።

አምባሳደር ኽርማን ኮህን በለንደን የተካሄደውንና የቀድሞ የደርግ መንግስት፣ ሕወሃት ፣ ሻዕብያና ኦነግ የተገኙበትን የለንደኑን ድርድር የመሩ መሆናቸው ይታወሳል።

የቀድሞው የአሜሪካ ዲፕሎማት አምባሳደር ኽርማን ኮኽን ይህንን አስተያየት የሰጡት አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን ኢትዮጵያ ደርሰው በተመለሱ ማግስት ነው።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አምባሳደር ዶናልድ ያማማቶ ምክንያቱ ግልጽ ባልሆነ ተልዕኮ ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ ደርሰው መመለሳቸው ይታወሳል።

የቀድሞው የአሜሪካ ዲፕሎማት ኽርማን ኮህን በ1983 ስልጣን ሲይዝ ተስፋ የጣሉበት የህወሃት/ኢህአዴግ ቡድን ከጠበቁት በታች እንደሆነና ከዘመኑ ጋር መጓዝ እንደተሳነው ሲገልጹ ቆይተዋል።

አምና በጥቅምት ወር ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የትግራይ የበላይነትና የይስሙላ ፌደራሊዝም ለኢትዮጵያ ቀውስ መንስኤ ሆነዋል ማለታቸው ይታወሳል።