የጋምቤላ ተወላጆች የተቃውሞ ሰልፍ ሳይደረግ ቀረ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 23/2011)በጋምቤላ ተወላጆች ዛሬ ተጠርቶ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ ሳይደረግ መቅረቱ ተገለጸ።

በሁለት ከተሞች ተጠርቶ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ ሳይካሄድ የቀረው አልተፈቀደም በሚል ምክንያት መሆኑን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ሰልፈኞች ገና ከመጀመራቸው በፖሊስ እንዲበተኑ መደረጉ ታውቋል።

በጋምቤላ ፍቃድ ተከልክሏል ለሌላ ጊዜ ጠይቁ በሚል የከተማው አስተዳደር ምላሽ መስጠቱን ነው የኢሳት ምንጮች የገለጹት።

በቅርቡ በፓርላማ የጸደቀውን የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ በመቃወም የተጠራውን ሰልፍ በኢትዮጵያ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ የጋምቤላ ክልል ተወላጆች አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወሳል።

በቅርቡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስድተኞችን ጉዳይ በተመለከተ በአብላጫ ድምጽ ያጸደቀውን አዋጅ በመቃወም ለዛሬ ተጠርቶ የነበረው ሰልፍ መቅረቱን በተመለከተ የጋምቤላ ክልል ካቢኔ የጻፈው ደብዳቤ ለጊዜው የተቃውሞ ሰልፉ እንዳይደረግ ውሳኔ መተላለፉን የሚገልጽ ነው።

በደብዳቤው እንደተመለከተው በጋምቤላ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የሚያስችል ምቹ ሁኔታዎች እስኪፈጠሩና ጉዳዩን በተመለከተ የግንዛቤ መድረክ እስኪመቻች ድረስ ለጊዜው ጥያቄውን መቀበል ተገቢ አይደለም ይላል።

የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት የተቃውሞ ሰልፉን በጠሩት የጋምቤላ ነዋሪዎችና በክልሉ መንግስት መካከል ሽማግሌዎች ገብተው ነበር።

የክልሉ አመራሮች የጸጥታና ሌሎች ጉዳዮች ምክንያታቸው እንደሆነ ቢገለጽም በካቢኔው የተጻፈው ደብዳቤ ላይ ለጊዜውም ቢሆን የተከለከለበትን ምክንያት አይጠቅስም።–አመቺውን ጊዜ እስክንገልጽላችሁ በትዕግስት እንድትጠባበቁ እንጠይቃለን ከሚለው የደብዳው ሃሳብ ውጪ

የተቃውሞ ሰልፉ አዘጋጆች የክልሉ መንግስትን ውሳኔ ተቀብለው ሰልፉን ማድረግ የሚችሉበትን ቀን በአስቸኳይ እንዲገለጽላቸው ጠይቀዋል።

በተመሳሳይ ዛሬ በአዲስ አበባ ተጠርቶ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍም ከጅምሩ በፖሊስ መቋረጡን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በመስቀል አደባባይ መሰባሰብ የጀመሩትን የተቃውሞ ሰልፉን ተሳታፊዎች ፖሊስ መበተኑን የገለጹት የኢሳት ምንጮች ሰልፉ ከከተማው መስተዳድር ፍቃድ አልተሰጠው የሚል ምክንያት መቅረቡንም ለማወቅ ተችሏል።

ከሃዋስ፣ ከአምቦ፣ ከአዲስ አበባና ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የተሰባሰቡት የጋምቤላ ክልል ተወላጅ የሆኑ ተማሪዎች በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀውን የስደተኞች ጉዳይ አዋጅን ለመቃወም ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱን አዘጋጆቹ ለኢሳት ገልጸዋል።

በፌደራል መንግስት ውስጥ የሚገኙ የጋምቤላ ተወላጅ የሆኑ ባለስልጣናት የአዲስ አበባው ሰልፍ እንዳይደረግ ውስጥ ለውስጥ ተንቀሳቅሰዋል ሲሉ አዘጋጁቹ ይወቅሳሉ።

መስተዳድሩ ሰልፉ እንደሚካሄድ የሚገልጽ ደብዳቤ እንዳልደረሰውም ይገልጻል።

አዲስ አበባ ገብተው ተቃውሟቸውን ለማሰማት መስቀል አደባባይ የተገኙት የጋምቤላ ክልል ተወላጅ የሆኑ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መንግስት የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ ዳግም እንዲከልሰው መጠየቃቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

አሁን ዘግይቶ በደረሰን ዜና ጋምቤላ ከተጠራው ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ጋር በተያያዘ ውጥረት ውስጥ ገብታለች።

የጸጥታ ሃይሎች ከተማዋን ባልተለመደ ሁኔታ ቁጥጥር እያደረጉ ሲሆን የወትሮው እንቅስቃሴ ቆሞ እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል።