ታህሳስ 28 ቀን 2004 ዓ/ ም
ኢሳት ዜና:-የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦሞት ኦባንግ አሎም “እኔ ከታሰርኩ መለስም ይታሰራል” በማለት በከፍተኛ የፌደራል ባለስልጣናት ፊት ተናግረዋል።
ተባባሪ ዘጋቢያችን አሰግድ ተፈራ እንደዘገበው የፌደራል መንግስት ባለስልጣናት ርዕሰ መስተዳደሩን በአኝዋክ ንፁሃን ጭፍጨፋ ወቅት የሚገደሉትን ሰዎች ስም ዝርዝር አዘጋጅተው አቅርበዋል በሚል ክስ መስርተውባቸዋል።
በክልሉ ነዋሪዎች “እውነተኛው ወያኔ” የሚል ስያሜ ያላቸው አቶ ኦሞት፣አቶ መለስ መታሰር አለባቸው በማለት የተናገሩት ከታህሳስ 23 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ በፌደራል መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት የሚመራ ግምገማ እተካሄደ ባለበት ወቅት ነው።
በግምገማው ላይ የተሳተፉ ታማኝ ምንጮች እንዳስታወቁት በክልሉ በሙስና ተዘርፏል በተባለ 80 ሚሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ፣ በብቃት ማነስ፣ ልማትን በማጓተትና በጎሳዎች ዕርስ በርስ ግጭት ሰበብ እየተካሄደ ባለ ግምገማ ላይ በድንገት ፕሬዚዳንቱ ከዛሬ ዘጠኝ ኣመት በፊት ለተካሄደው ጭፍጨፋ ተጠያቂ መደረጋቸው የክልሉን ባለስልጣናትና የፖለቲካ አመራሮች አስገርሟል።
አስገምጋሚው ባለስልጣን “በጋምቤላ የተገደሉትን የአኙዋክ ጎሳዎች ስም ዝርዝር አዘጋጅተህ ያቀረብከው አንተ ነህ ትታሰራለህ” በማለት ሲናገሩ ግምገማው ላይ የተገኙ ባለስልጣናት የመደናገር ስሜት ታይቶባቸው ነበር።
እኣአ 2003 በጅምላ ለተጨፈጨፉት የአኝዋክ ምሁራንና ንጹሃን ዜጎች ወንጀለኛ የተደረጉት ፕሬዚዳንቱ የሰጡት መልስ ደግሞ አስደንጋጭ እንደሆነባቸው ምንጮቹ አስረድተዋል።
“እኔ” አሉ ፕሬዚዳንቱ ኦሞት ኦባንግ፣ “እኔ ከታሰርኩ ወታደርና መሳሪያ የሰጠኝ አቶ መለስም ይታሰራል” የሚል መልስ ሰነዘሩ።
መረጃ በማስደገፍ የግምገማውን ድራማ ያስረዱት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የክልሉ አንድ ባለስልጣን “የህወሃት ታማኝ በመሆን የሚታወቁት አቶ ኦሞት ላይ እየተካሄደ ያለው ግምገማ መድረሻው አጓጉቶኛል” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
አቶ ኦሞት ሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ እንደተማሩ፣ የክልሉ የደህንነት ሐላፊ ሆነው ማገልገላቸውንና ፕሬዚዳንት ሆነው ከመመረጣቸው በፊት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር እንደነበሩ ግለ ታሪካቸው ያስረዳል። ይህንኑ ጠቅሰው ከህወሃት ጋር የነበራቸውን የጠበቀ ትስስር ያመለከቱት ምንጮቻችን ስለግምገማው ዓላማና መድረሻ ያሰባሰቡትን መረጃ ዘርዝረዋል።
አቶ መለስ በጋምቤላ የአኝዋክ ንጹሃን ላይ በተካሄደው ጭፍጨፋ ከፍተኛ ውግዘት ደርሶባቸዋል። ‹‹የዓለም አቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC)ና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ጉዳዩን እያጠናከሩት ይገኛሉ›› ያሉት የመረጃው ምንጮች መለስ በወቅቱ የተጠቀሙባቸውን ሰው የወንጀሉ ተጠያቂ በማድረግ ከውንጀላው ነጻ ለመውጣት የነደፉት ስልት መሆኑን ያስረዳሉ።
በሌላም በኩል መለስ ክፉኛ እየተተቹ ያለበትና ገበናቸውን እያጋለጠው ያለው የመሬት ነጠቃ (land grabbing) የሚካሄደው በጋምቤላ በመሆኑ፣ የአገሬውን ተወላጅ በማፈናቀልና ለባርነት ተላልፈው እንዲሰጡ ማድረጋቸው በከፍተኛ ደረጃ ስማቸውንና አስተዳደራቸውን ስላጎደፈው ፣ ለጎደፈው ስማቸው ማደሻ የሚጠሉትን አቶ ኦሞትን የመስዋዕት በግ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ይናገራሉ። አቶ ኦሞት ላይ በመፍረድ “ከደሙ ንጹህ ነኝ” ለማለት መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።
በሶስተኛ ደረጃ የሚቀርበው ትንተና በክልሉ ያለውን የደራ የመሬት ችብቸባ ገበያ ለመቀጠል በክልሉ አስተማማኝ ሰላም ያስፈልጋል። ካራቶሪ፣ ሳውዲ ስታርና ሼክ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ ለጀመሩት እርሻ ስጋት የሆኑ የአኝዋክ ወጣቶችን አባብሎ ከሸፈቱበት ጫካ እንዲወጡ ለማድረግ አቶ ኦሞትን የጅምላ ጭፍጨፋው ተጠያቂ ማድረግ ዋና ስልት ተደርጎ መወሰዱን የዜናው ምንጮች አስረድተዋል።
በዋናነት ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች ሳቢያ የአቶ ኦሞት የስልጣን ዘመን ማክተሙን የሚናገሩት ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ክፍሎች ለጋምቤላ ሰባተኛ ፕሬዚዳንት መዘጋጀቱን አመልክተዋል። ህወሃት ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ አራት ፕሬዚዳንቶች ግልጋሎታቸውን ካበረከቱ በሁዋላ ለእስር ሲዳረጉ አምስተኛው ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ኦኬሎ አኳይ ተሰደዋል።
አቶ ኦኬሎ አኳይ የ2003ቱን የጅምላ ጭፍጨፋ አስመልክቶ ለሂዩማን ራይትስ ዎች የተሳሳተ መረጃ እንዲሰጡ በአቶ አባይ ጸሃዬና ገብረአብ ባርናባስ ታዘው ነበር።ፕሬዚዳንቱ በወቅቱ ይፋ እንዳደረጉት ግጭቱ የጎሳዎች የርስ በርስ እንደሆነ፣ አንድ ሰው ሲቆስል 59 ሰዎች መሞታቸውንና አንድ ቤት ብቻ መቃጠሉን ሪፖርት እንዲያደርጉ ታዘው ባለመቀበላቸው ህይወታቸው አደጋ ላይ በመውደቁ ለመሰደድ ተገደዋል።
አቶ ኦሞት በተመሳሳይ ሊኮበልሉ ይችሉ እንደሆነ ለተጠየቁት አስተያየት ሰጪዎቹ “አይሆንም። ጭፍጨፋውን አምልጠው ሱዳን ያሉ፣ በስደት ኬኒያ የገቡ የአኙዋክ ሰዎች አይፈቅዱላቸውም” የሚል ድፍን መልስ ሰጥተዋል። አቶ ኦሞት ለሰሩት ውለታ በ2005 ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ መደረጋቸውን የአኝዋክ ፍትሕ ምክርቤት (Anuak Justice Council) ጥቅምት 5፣2005 (እአአ) በድረ ገጹ ዘግቧል። ድረገጹ በዘገባው በጋምቤላ በተካሄደው ጭፍጨፋ አጃቸው እንዳለበት የተጠቆመው የፌደራል ደህንነት ከፍተኛ ባለስልጣን አቶ አለማው አላምሩ መስከረም 25፣2005 ጋምቤላ በመሄድ “የመንግስትን ፖሊሲና እቅድ መተግበር የሚችል ብቸኛ ሰው አቶ ኦሞት ነው” በማለት መናገራቸውን ገልጿል።
በመዠንገር፣ ኑዌርና አባል በሆኑበት የአኙዋክ ጎሳ ተቀባይነት እንደሌላቸው የሚነገርላቸው አቶ ኦሞት፣ ሰኔ 7፣2008 ካናዳ ከአኝዋክ ብሄረሰብ አባላት ጋር ሊያደርጉት የነበረው ውይይት የካናዳ መንግስት የመግቢያ ቪዛ ስለከለከላቸው ሳይሳካ መቅረቱን የካናዳ ድረገጽ (www.canada.com) በተመሳሳይ ቀን ዘግቦታል። በዘገባው የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ “በሰብአዊ መብት ጥሰት የተወነጀለ ሰው ኢትዮጵያዊያንን ሰብስቦ የማነጋገር መብት የለውም” የሚል አስተያየት መስጠታቸውን አስፍሯል።
ግምገማው ሲጠናቀቅ ምን እንደሚወሰን የዜናው ምንጮች ግምት ከመስጠት ተቆጥበዋል። ስለጉዳዩ ያነጋገርናቸው አቶ ኦባንግ ሜቶ ግን “አቶ ኦሞትን በተመለከተ እየተካሄደ ስላለው ግምገማ በቂ መረጃ አለን። በግፍ ለተጨፈጨፉት የአኝዋክ ንጹሃን ዜጎች የፍርድ ሂደት ጠቃሚ ግብአቶች አግኝተናል። የቀን ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር አቶ መለስም ሆኑ ሌሎች በድርጊቱ የተሳተፉ ለፍርድ ይቀርባሉ። ኢትዮጵያም ፍትህ ታገኛለች” በማለት በእጃቸው ስለገባው መረጃ በዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል።