የገደንቢ ወርቅ ማምረቻ የሚያደርሰው ማህበራዊ ቀውስ መባባሱ ተገለጸ

 

(ኢሳት ዜና–ታህሳስ 2/2010) ለገደንቢ ወርቅ ማምረቻ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ያመጣው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ተባብሰው መቀጠላቸውን ቢቢሲ ገለጸ።

ኩባንያው ወርቁን ለማጽዳት የሚጠቀምበት “ሳናይድ”የተባለው ኬሚካል የልብ፣የአእምሮና የነርቭ ህመሞችን እንደሚያስከትል ሙያተኞቹ ገልጸዋል።

ሜድሮክ ወርቅ ማዕድን ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ለገደንቢ ወርቅ ማምረቻ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ያመጣው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ተባብሰው መቀጠላቸውን ቢቢሲ በዘገባው አመልክቷል።

የሚዲያ ተቋሙ በአካባቢው በአካል በመገኘት የሻኪሶ ነዋሪዎች፣የጤና ባለሙያዎች፣የወረዳው ሃላፊዎችንና የሚመለከታቸው የመንግስት ባለስልጣናትን አናግሯል።

ዘገባውንም “ኦዶ ሻኪሶ ወርቅ መርዝ የሆነባት ምድር” ሲል አጠናቅሮታል።

የኦዶ ሻኪሶ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ የሆኑት አቶ ጦና ዋሬ ሲናገሩ ሜድሮክ ወርቁን ለማጽዳት የሚጠቀምበት “ሳናይድ” የሚባለው ኬሚካል በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የራስ ምታት፣የልብ፣የአእምሮና የነርቭ ህመሞችን በማስከተል ላይ ይገኛል።

ኬሚካሉ የሰው አጥንትን ለማጠናከር የሚረዱ እንደ ብረት ያሉ ንጥረ ነገሮችን ከሰው አካላት ላይ በመቀነስ ለአጥንት መሳሳትና መሰባበር ማጋለጡን አክለው ተናግረዋል።

ነፍሰጡር ሴቶች ያስወርዳቸዋል፣ሕጻናት ሲወለዱ ካለጭንቅላት ይወለዳሉ፣ጭንቅላታቸው መጠኑ በጣም ያነሰ ይሆናል፣እጅና አይናቸው ተጎድቶ ይወለዳሉ፣ሰው ታሞ ወደ ሀኪም ቤት ሲሄድ ከነርቭ ጋር የተያያዘ ችግር ነው ይባላል።

በአካባቢው የአካል ጉዳተኞች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ መሄዱንም የጽህፈት ቤት ሃላፊው ጨምረው ገልጸዋል።

በህጻናት ላይ የሚደርሰው የአካል ጉዳት በቀበሌው ውስጥ በፍጥነት እያደገ በመምጣቱ ነዋሪዎቹ ወልደው ለመሳም እንኳን እየተሳቀቁ መሆኑን ነዋሪዎች በአካል ለተገኘው የቢቢሲ ሪፖርተር ተናግረዋል።

ነፍሰጡር እናቶች ልጃቸውን ወልደው ከአካል ጉዳት ነጻ መሆኑን እስኪያረጋግጡ ድረስ ማርገዛቸውን እንደሚደብቁ፣የአካል ጉዳት ያለበትን ሕጻን የወለዱ እናቶችም ከሰው አይን ከልለው በቤት ውስጥ ደብቀው እንደሚያሳድጓቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የሳናይድ ኬሚካል የተቀላቀለበት ወራጅ ውሃ የሚጠጡ እንስሳት ወዲያውኑ እንደሚሞቱ፣የተበከለ አየር ውስጥ የሚቆዩት ደግሞ ከወደቁ በኋላ መነሳት እንደማይችሉ አጥንታቸው በቀላሉ እንደሚሰበር የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል።

በዚህ ችግር የተነሳ በከብቶችና በዱር እንስሳት ላይ እየደረሰ ያለው እልቂት ለችግር እንዳጋለጣቸው ተናግረዋል።

የሼህ መሃመድ አላሙዲን ንብረት የሆነው ለገደንቢ ወርቅ ማምረቻ ከሚያስከትለው ጉዳት ውጪ ለአካባቢው ምንም የጠቀመው ነገር የለም ይላሉ የሻኪሶ ነዋሪዎች።

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ከወርቅ ማምረቻው የስራ እድል እንኳን እንደማያገኙ በምሬት ገልጸዋል።

በከተማዋ ከስምንት አመት በፊት የተጀመረው የአስፋልት መንገድ እስካሁን እንዳልተጠናቀቀ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

የሜድሮክ የወርቅ ማዕድን በ1998 የለገደንቢን የወርቅ ማዕድን ከመንግስት እጅ በ172 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ለ20 አመታት በሊዝ መውሰዱን ቢቢሲ በዘገባው አመልክቷል።

ኩባንያው በ16 አመታት ውስጥ ባመረተው የወርቅና የብር ማዕድን ከ17 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱንም ለማወቅ ተችሏል።

ድርጅቱ ለ20 አመታት የተፈራረመው ውል ከአንድ ወር በኋላ የሚጠናቀቅ በመሆኑ በድጋሚ እንዲታደስለት ማመልከቻ ማስገባቱ ተገልጿል።

ኢሳት የአካባቢውን ነዋሪዎች፣ሙያተኞችንና ጋዜጠኞችን በማናገር የለገደንቢ ወርቅ ማምረቻ በህብረተሰቡ፣በቤት ውስጥና የዱር እንስሳት ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት በተደጋጋሚ መዘገቡ የሚታወስ ነው።