ሕወሃት በስብሰባ ተጠምዷል ተባለ

(ኢሳት ዜና–ታህሳስ 2/2010)

ፎቶ ፋይል

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በስብሰባ መወጠሩ ተሰማ።

ሕወሃት በአቶ አባይ ወልዱና ወይዘሮ አዜብ መስፍን ምትክ አቶ ጌታቸው ረዳንና ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂምን እንዲሳተፉ ማድረጉ ታውቋል።

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ የውጭ ሀገር ጉዟቸው ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ተሰርዟል።                                  

በማያቋርጥ ስብሰባ የተጠመደው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በሀገራዊ፣ወቅታዊና ድርጅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመወሰን በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት መሰብሰቡን ለማወቅ ተችሏል።

የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በሕወሃት ንብረትነት ለተያዘው ፋና ብሮድካስቲንግ እንደተናገሩት የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከሌሎች ጊዜያቶች በተለየ መልኩ ጠንካራ ውሳኔ ሊያሳልፍ ይችላል።

ከሌሎች ጊዜያቶች በተለየ የሚተላለፈው ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል ከመጥቀስ ተቆጥበዋል።

ሕወሃት የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አባይ ወልዱንና የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ባለቤት ወይዘሮ አዜብ መስፍንን በማስወገድ ሌሎችን በምትካቸው ይዞ ስብሰባውን እያካሄደ መሆኑ ታውቋል።

በዚህም የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ስብሰባ፣ከድንበር ግጭቶች ጋር በተያያዘ ተጠያቂ የተባሉ ባለስልጣናት እንዲታሰሩ የሚያዝ ውሳኔ ሊተላለፍ እንደሚችል በፖለቲካ ምሁራን ዘንድ ግምት ተቀምጧል።

ከድንበር ግጭቱ ጋር በተያያዘ በሕወሃትና በኦህዴድ መካከል ባለው የአቋም ልዩነት ዙሪያ ውሳኔ ማሳለፉ ቀላል እንደማይሆንም ተመልክቷል።

በኦሮሚያና ኢትዮጵያ ሶማሌ አዋሳኝ ግጭት ኦህዴድ ተከላካይና ተጠቂ ነኝ የሚል አቋም በመያዙ በሕወሃት በኩል ከሁለቱም ወገን ከፍተኛ ሃላፊዎችን ለማሳሰር የተያዘው እቅድ ውሳኔ ማግኘቱ አጠራጣሪ ሆኗል።

ከዚህም በተጨማሪ በሕወሃት በኩል በኦሮሚያ ለቀጠለው ግጭት ከፍተኛ የኦህዴድ መሪዎችን በተለይም አቶ አባዱላ ገመዳን ጨምሮ የተወሰኑ ባለስልጣናትን ተጠያቂ የማድረግ ፍላጎት መኖሩንም ምንጮች ይገልጻሉ።

አሁን ባለው የኦህዴድ ቁመናና ሕዝባዊ ድጋፍ ሕወሃት የማስወሰንና የማስተግበር ፈተና ይገጥመዋል ሲሉ ምንጮቹ ያክላሉ።

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ በዩኒቨርስቲዎች ለቀጠለው ዘርን መሰረት ያደረገ ግጭትን በተመለከተም ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።

በዚህ ዙሪያ ዝርዝር ውሳኔው ምን እንደሆነ ባይታወቅም የዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንቶችና ሌሎች ሃላፊዎች በየክልላቸው የሚመደቡበት ሁኔታ እንዲቀር፣እንዲሁም ስፍራውን በውድድር እንዲይዙት ለማድረግ መታቀዱም ተሰምቷል።

በዚህ ረገድ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በአምባሳደርነት ሹመት ስፍራውን በለቀቁት በዶክተር አድማሱ ጸጋዬ ምትክ ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩ ማመልከቻ እንዲያስገቡ ጥሪ ማቅረቡና ይህም እስከሚቀጥለው ሰኞ ድረስ እንደሚቆይም ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ የውጭ ሀገር ጉዟቸው ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ተሰርዟል።

የኦህዴድ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ድሪባ ኩማ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህራን ጋር ቅዳሜ ህዳር 30/2010 ምሽት ከአዲስ አበባ ወደ ዋሽንግተን ማቅናት የሚጠበቅባቸው ቢሆንም ሌሎቹ ከሳቸው ጋር ይጓዙ የነበሩት ልኡካን ጉዟቸውን ሲቀጥሉ እሳቸው ግን መቅረታቸው ታውቋል።

አንዳንድ ምንጮች እንደገለጹት ከሀገር እንዳይወጡ በመወሰኑ አቶ ድሪባ በጉዞው ሳይሳተፉ ቀርተዋል።

ሌሎቹ ልኡካን እሁድ ታህሳስ 1/2010 ዋሽንግተን ዲሲ አውሮፕላን ማረፊያ ከደረሱ በኋላ ዛሬ ወደ ዳላስ ቴክሳስ ማቅናታቸው ታውቋል።