የገቢዎችና የጉምሩክ ባለስልጣን ዋና እና ምክትል ዳይሬክተሮችን ጨምሮ 16 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መንግስታዊ መገናኛ ብዙሀን ዘገቡ

ግንቦት ፫(ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ቀደም ሰል የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩትና ሚኒስቴሩ በበለስልጣን መስሪያ ቤት ሆኖ ሲዋቀር ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት አቶ መላኩ ፋንታ፣ ምክትል ዳይሬክተሩ አቶ ወልደዋህድ ገብረጊዮርጊስ እና ሌሎች ከ 10 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት በሙስና ተጠርጥረው እንደሆነ መንግስት ገልጿል።

የ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዜና አቅራቢ አጠቃላይ የታሰሩት ሰዎች 12 መሆናቸውን ሲገልጽ፤ዝርዝር ዜናውን ያነበበው ሪፖርተር ታሳሪዎቹ 16 መሆናቸውን ነው በዘገባው ያቀረበው።

ሁለቱን ባለስልጣናትና ከነሱ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉት ሰዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ክስ የመሰረተውም፤የፌዴራሉ የጸረ ሙስና ኮሚሽን እንደሆነ ተመልክቷል።

ከሁለቱ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር በቁጥጥር ስር እንዲውሉ የተደረጉት ግለሰቦች እሸቱ ወልደሰማያት – በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የአቃቤ ህግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ፣ አስመላሽ ወልደማሪያም- የቃሊቲ ጉምሩክ ኃላፊ ፣ ጥሩነህ በርታ- በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የተወረሱ ንብረቶች አስተዳደር ቡድን መሪ ፣ አምኘ ታገለ- የናዝሬት ጉምሩክ ኃላፊ ፣ ሙሉጌታ ጋሻው- በኦሮሚያ ልዩ ዞን መሀንዲስ ፣ ከተማ ከበደ- የኬኬ ትሬዲንግ ባለቤት ፣ ስማቸው ከበደ- የኢንተርኮንቴንታል ሆቴል ባለቤት ፣ምህረት አብ አብርሀ- ባለሀብት፣ነጋ ገብረእግዚአብሄር- የነፃ ትሬዲግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤት ፣ ዘሪሁን ዘውዴ -ትራንዚተርና ደላላ ፣ማርሸት ተስፉ – ትራንዚተርና ደላላ ናቸው፡፡

ኮሚሽኑ ባለስልጣናቱን እና ሌሎቹን ግለሰቦች  በፖሊስ ስር እንዲውሉ ያደረጋቸው ከብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር ነው ተብሏል።

ከሁለቱ ባለስልጣናት በተጨማሪ ሌሎች የጉምሩክ ሰራተኞች እና በንግድ ሥራ የተሰማሩ ግለሰቦች ናቸው የታሰሩት-እንደ መንግስት መገናኛ ብዙሀን ገለፃ።

ሁሉም ታሳሪዎች በቁጥጠር ስር የዋሉት የፍርድ ቤት ማዘዣ ከወጣባቸው በሁዋላ እንደሆነም ተገልጿል።

በብዙሀን መገናኛዎቹ የተባለው እውነት ከሆነ ፤ከተመሰረተ 11 ዓመታት ያለፈው ጸረ-ሙስና ኮሚሽን በሚኒስትር ደረጃ ከፍተኛ ባለስልጣናትን በሙስና ወንጀል ሢከስ የይህ የመጀመሪያው ይሆናል።

ኮሚሽኑ ከ ዓመት በፊት 10ኛ ዓመት የምስረታ በ ዓሉን በሂልተን ሆቴል ሲያከብር ጥናት ያቀረቡ አንድ የ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁር፤ ኮሚሽኑ ባለፉት ዓመታት ጉዞዎቹ በሙስና ካስቀጣቸው ከ 500 በላይ ሰዎች መካከል አንድም ስም ያለው ባለስልጣን እንደሌለ በመጠቆም፤ በማጠቃለያቸው ፦<<ይህም የጸረ-ሙስና ኮሚሽን ባለስጣናትን እንደሚፈራ የሚያመላክት ነው>> ማለታቸው ይታወሳል።

ኢሳት አስተያየታቸውን የጤቃቸው የብዙሀን መገናኛዎቹን ዜና ያደመጡ ሰዎች ፤<<  ሚኒስትር መላኩ ፋንታና ሌሎቹ ታሳሪዎች በቁጥጥር ስር የዋት በሙስና ነው ብሎ ለማመን ይቸግራል። አስተያየት ለመስጠትም ነገሩን ትንሽ ማየት ያስፈልጋል>> ብለዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ ከመገናኛ ብዙሀኑ ዜና ግራ ያጋባቸው፦”ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ታሳሪዎቹን በቁጥጥር ያዋላቸው ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር ነው” የሚለው ገለፃ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት በጋዜጠኞች፣በተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እና በ ሙስሊም መሪዎች እና በሌሎች የ ኢህአዴግ ተቀናቃኞች ላይ የፈጠራ የሽብርተኝነት ክስ በመመስረት የሚታወቅ አፋኝ ተቋም መሆኑ ይታወቃል።