(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 28/2010) በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በጌዲዮዎች ላይ የደረሰው ጥቃትና መፈናቀል ትኩረት ተነፍጎታል በማለት የዲላ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት በተቃውሞ ስልጣናቸውን ለቀቁ።
700 ሺ ያህል ዜጎች የተፈናቀሉበት፣ብዙዎች የተገደሉበትና የቆሰሉበት የጉጂ ዞን ግጭት በሽምግልና እንደተፈታ ቢገለጽም ችግሩ ግን መፍትሔ አለማግኘቱ ተመልክቷል።
ወራት ላስቆጠረው የጌዲዮዎች መፈናቀልና ግድያ የፌደራል መንግስትም ሆነ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በቂ ትኩረት አልሰጠም ብለዋል የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ቃልኪዳን ነጋሽ።
በዚህም ምክንያት ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን አስታውቀዋል።
ዶክተር ቃልኪዳን ነጋሽ ለዋዜማ ሬዲዮ በሰጡት መግለጫ በዜጎች ላይ ከሚደርሰው መፈናቀል ባሻገር በዩኒቨርስቲው ውስጥ የሚታየው ብሔርን መሰረት ያደረገ ማጥላላት ጥሩ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
ባለፈው ሰኔ መጀመሪያ ላይ በዩኒቨርስቲው የደረሰው የቦምብ ጥቃትም ስልጣናቸውን እንዲለቁ ምክንያት እንደሆናቸውም አስታውቀዋል።
በቦምቡ ጥቃት ዙሪያ መረጃዎች እንዲድበሰበሱ መደረጋቸው ስጋት ውስጥ እንደከተታቸውም አስታውቀዋል።