የደደር ወረዳ ወጣቶች የጦር መሳሪያዎችን በመቀማትና መንገድ በመዝጋት ተቃውሞ እያደረጉ ነው
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 17 ቀን 2010 ዓ/ም) የአካባቢው ወኪላችን እንደገለጸው ትናንት በምስራቅ ሃረርጌ ወረዳ ማጫ ቀበሌ ማህበር የሚገኙ ወጣቶች እራሳቸውን በማደራጀት በአካባቢው ከሚገኙ የሚሊሺያ አባላት ላይ የጦር መሳሪያዎችን በመንጠቅና አካባቢውን በድንጋይ በመዝጋት ተቃውሞ እያደረጉ ነው። ወጣቶቹ የቀሙትን የጦር መሳሪያው እንዲመልሱ እንዲሁም ተቃውሞአቸውን እንዲያቆሙ ለማሳመን የተላከው የኦሮምያ ፖሊስና የክልሉ አድማ ብተና ሃይል፣ ከአቅሙ በላይ የሆነበት መሆኑን ገልጾ ሪፖርት በማድረጉ፣ በምስራቅ ሃረርጌ የተዋቀረው ወታደራዊ እዝ ተጨማሪ ሰራዊት ወደ አካባቢው ልኳል። ውጥረቱ ይህን ዜና እስካጠናከርንበት እኩለ ቀን ድረስ ቀጥሎ ውሎአል።
በሌላ በኩል የኦህዴድ ነባር አመራሮች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስፈላጊ መሆኑን ህዝቡን እንዲሰብኩ ታዘው ለ10 ቀናት ወደ ወረዳዎች ወርደው ህዝቡን ሊያነጋግሩ መሆኑ ታውቋል። አመራሮቹ የኢህአዴግ ስብሰባ ውጤቱ ሳይታወቅ አንሄዱም ቢሉም፣ ማእከላዊነትን ትጥሳላችሁ በሚል ታዘው መውረዳቸው ታውቋል።
ባለስልጣናቱ በየወረዳው እየተገኙ ነጋዴዎችን ፣ ታዋቂ ግለሰቦችን የአገር ሽማግሌዎችን ያነጋግራሉ። ከህዝቡ ጋር በሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ የገለጹት ምንጮች፣ አንደኛው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስፈላጊነት በተመለከተ ይሆናል። ኦህዴድ አዋጁ አያስፈልግም የሚል አቋም ሲያራምድ መታየቱን ተከትሎ፣ ህዝቡም አዋጁ አያስፈልግም የሚል አመለካከት እየያዘ ነው በሚል እምነት የኦህዴድ ከፍተኛ አመራሮች ወደ ህዝብ ወርደው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስፈላጊነት ለህዝብ እንዲያስረዱ ፣ አህዴድ እንደ ደርጅት አዋጁን እንደሚደግፍ እንዲገልጹ ታዘዋል።
ሌላው ህዝቡን የማሳመን ስራ እንዲሰሩ የተዛዙት ኦህዴድ ከኦነግና ከሌሎችም አገር ውስጥ ካሉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር አንድ ሆኗል የሚለውን አመለካከቱን እንዲቀይር ማድረግ ነው። ኦህዴድ ከተቃዋሚዎች ጋር ለመነጋገርና ዝግጁ ነኝ ብሎ ማስታወቁን ተከትሎ ህዝቡ ኦህዴድን ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር አብሮ ደምሮ ማየቱን እንዲያቆም ለማድረግ፣ ኦህዴድ ለኦሮሞ እና ለኢትዮጵያ ህዝብ ይጠቅማል ብሎ በማሰብ ከተቃዋሚዎች ጋር እነጋገራለሁ ማለቱን ይህ ማለት ግን ኦህዴድና ተቃዋሚዎች አንድ ናቸው ማለት እንዳልሆነና ልዩነት እንዳላቸው እንዲያስረዱ መታዘዛቸው ታውቋል።
የኦህአዴድ ባለስልጣናት ከማእከላዊ የተላከ ነው የተባለ የማወያያ ጽሁፍ ተሰጥቷቸዋል። ወደ ወረዳዎች የሚወርዱት ባለስልጣናት “አሁን ህዝቡን የማወያያ ጊዜ ነው ወይ? ህዝቡ ኦህዴድን ለመደገፍም ሆነ ላለመደገፍም የኢህአዴግን የምክር ቤት ስብሰባ እየተከታለ ነው፣ ይህ አንድ ነገር እልባት ሳያገኝ በተለይም ጠ/ሚኒስትሩ ከኦህዴድ ሳይሆን ከቀረ የሚፈጠረው አደጋ ሳይታወቅ እንዴት ውረዱ እና አወያዩ እንባላለን ?” በማለት ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ማእከላዊነትን ጠብቁ ተብለው በመታዘዛቸው ሳይወዱ በግድ ወደ ወረዳዎች እየወረዱ ነው። ኦህዴድ የጠ/ሚኒስትርነት ቦታው ካልተሰጠው ፣ ህዝቡ አምኖ አይከተለንም በሚል እምነት የጠ/ሚኒስትርነት ቦታው እንዲሰጠው ግፊት እያደረገ ነው።
ኢህአዴግ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የምክር ቤት ስብሰባውን አጠናቆ የድርጅቱን ሊ/መንበርና የአገሪቱን ጠ/ሚኒስትር ያሳውቃል ተብሎ ቢመጠበቅም፣ በድርጅቶች መካከል በተፈጠረው ውዝግብ ሳይሳካለት ቀርቷል። በተለይ የኦህዴድ ባላስልጣናት የአብዮታዊ ዲሞክራሲን መርሆዎች መቀበል አቁመዋል በሚል ህወሃት እና እንደ አቶ በረከት የመሳሰሉ የብአዴን ሰዎች ኦህዴድ የጠ/ሚኒስትርነርት ቦታው እንዳይሰጠው ለማሳመን ሲጥሩ ሰንብተዋል። በዚህም የተነሳ ማእከላዊ ኮሚቴው ስብሰባውን ማጠናቀቅ እንደተሳነው ምንጮች ይገልጻሉ።