የደቡብ ክልል ተወላጅ መምህራን “በ25 አመታት አንድ ጀኔራልን ማፍራት ያልቻልነው ለምንደነው?” ነው ሲሉ ጠየቁ

ታኀሳስ ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሃረማያ ዩኒቨርስቲ ተጠርቶ በነበረው ስብሰባ ላይ የደቡብ ክልል መምህራን ” አሁን ስለሰላም ፣ ስለመልካም አስተዳደርና ስለልማት ብታወሩ ማን ይሰማችሁዋል? እኛ ባለፉት 25 ዓመታት አንድ ጄኔራል ማፍራት ያቃተን ምን ስለሆንን ነው?” ሲሉ ጥያቄ አቀርበዋል። በአንድ የህወሃት መሪና በዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት የተመራው ስብሰባ ከፍተኛ ጭቅጭቅ የታየበት እንደነበር ዘጋቢያችን ገልጿል።
ከደቡብ ክልል የመጡ መምህራን ስሜታዊ ሆነው ጥያቄዎችን እና አስተያየቶችን ይሰጡ እንደነበር የገለጸው ዘጋቢያችን፣ በተለይ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ያለው የስልጣን ክፍፍል ጥያቄ ዋና አጀንዳው ነበር። “ጄኔራል የሚወለደው ከአንድ ክልል ብቻ ነው ወይ?” ያሉት መምህራን ፣ መሰረታዊ የሆነውን የስልጣን ጥያቄ ሳትፈቱ ስለሌሎች ጉዳዮች ብታወሩ የሚሰማችሁ የለም ብለዋል።
ፕሮፌሰር ጨመዳ ጣልቃ ገብተው፣ ሁኔታዎችን ለማስተካከል እየተሰራ በነበረበት ሰአት የኦሮሞ ተማሪዎች ጥያቄ መነሳቱን በመግለጽ ለማብረድ ቢሞክሩንም መምህራኑ ግን የሚመለሱ አልነበሩም።