የደቡብ ነዋሪዎች በኑሮዋቸው መጎሳቆላቸውን ገለጹ

መስከረም ፱(ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በደቡብ ክልል በቆላማና ከፊል  ቆላማ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ  አርብቶአደሮች ባለፉት 20 ዓመታት በአካባቢው በተደጋጋሚ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ለከፍተኛ ጉስቁልና መዳረጋቸው ታውቋል።

በቦረና ዞን ብቻ በ2005 ዓ.ም 30 ሺህ 216  እንስሳት  በድርቅ  ሲያልቁ፣  በ2004 ዓ.ም ደግሞ 10 ሺህ 609 እንስሳት አልቀዋል፡፡

በማኅበራዊ ጥናት መድረክ የአካባቢ ጉዳዮች ተመራማሪ የሆኑት አቶ  አለባቸው አደም  ከመልካም አስተዳደርና ከአየር ጸባይ ለውጥ ጋር  በተያያዘ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ማለትም በቦረና፣ በጉጂ እና በደቡብ ኦሞ በሚገኙ ስድስት ወረዳዎችና ስምንት ቀበሌዎች እየተከሰቱ ባሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ላይ ሁለት ዓመታትን የፈጀ ጥናት አካሂደዋል፡፡ የጥናቱን መነሻና ግኝቶች አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎች  በከፋ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ድህነት  ውስጥ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ከአቅም በላይ በሆነ ግብር የተነሳ ነዋሪዎቹ ህይወታቸውን ለመምራት በማይችሉበት ደረጃ እየደረሱ ነው ብለዋል ባለሙያው።

ጥናቱ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ቀደም ሲል ያልነበሩ የተለያዩ የሰውና የእንስሳት በሽታዎች  መከሰታቸውም ታውቋል።   ወባ ቀደም ሲል የአካባቢው  ኅብረተሰብ ቀለል አድርጎ የሚያየው  በሽታ የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ጊዜ ግን ሰው ታሞ  የማይድንበት  ሁኔታ  መፈጠሩ ተመልክቷል፡፡   በ ደቡብ ኦሞ 77 በመቶ ያህሉ ሕዝብ ለወባ የተጋለጠ ነው፡፡ 61 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ ደግሞ ለቆላ ዝንብ በሽታ የተጋለጠ ነው፡፡  በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች ኅብረተሰቡ በሽታን የሚቋቋሙ  ግመልና  ፍየሎችን እንዲያረቡ  ቢያበረታቱም፣ ግመሎች  ባልታወቀ  በሽታ በመጠቃታቸው በወር እስከ 3 ሺ ግመሎች ማለቃቸው ታውቋል።

አንድ እናት ግመል እያለቡ በነበረበት ወቅት ግመሏ በላዩዋ ላይ በመውደቋ ግመሏም ሴትዮዋም ወዲያውኑ ህይወታቸው አልፏል።

፡በመንግሥት  የቤተ  ሙከራ  ምርመራ እንዲካሄድ በመፍቀዱ ናሙናው ወደ ውጪ አገር ተልኮ  ውጤት  እየተጠበቀ  ነው፡፡

ባለፉት  20  ዓመታት  በቦረና ብቻ የአንድ አርብቶ አደር የእንስሳት ሐብት  ከ10  በሬ  ወደ  ሦስት    ከ35  ላሞች  ወደ ሰባት ፣ ከ33 ፍየሎች ወደ ስድስት አሽቆልቁሏል፡፡ በደቡብ ኦሞ ከ30 ላሞች ወደ 20፣ ከ38 ፍየሎች ወደ 23 ከ36 በጎች ወደ 21 ያሽቆለቆለበት ሁኔታም ተፈጥሯል፡፡ ከዚህ ችግር ጋር በተያያዘ በቦረና ዞን ብቻ ከ2000 ዓ.ም እስከ 2005 ዓም  44 በመቶ ያህል ሕዝብ ዕርዳታ ፈላጊ ሆኖ ቆይቷል።

መንግስት የገበሬውን ህይወት መለወጡን የተመለከተ ዘገባ በየጊዜው ቢያሰራጭም፣ በመሬት ላይ ያለው እውነታ ከዚህ የተለየ መሆኑን የመስኩ ባለሙያዎች ይናገራሉ።