ተቃዋሚዎች በመስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ እንዳያደርጉ ተከለከሉ

መስከረም ፱(ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- መስከረም 12 እና መስከረም 19 ሰማያዊ እና አንድነት ፓርቲዎች በተከታታይ የጠሩዋቸው ሰልፎች በመስቀል አደባባይ እንደማይካሄዱ የአዲስ አበባ መስተዳድር ህዝባዊ ስብሰባ ማስታወቂያ ክፍል አስታውቋል።

ጽህፈት ቤቱ ይህን ያስታወቀው ከሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ጋር ውይይት ካደረገ በሁዋላ ነው።

ይህንን ውሳኔ ተከትሎ ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ” ህዝባዊ አገልግሎት የሚሰጥ ቦታ ለዜጎች ሁሉ መብት የሆነውን ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት በህግ ለተቋቋመና ህዝባዊ ሀላፊነትን ለወሰደ የፖለቲካ ፓርቲ መከልከልና እስከዛሬም ድረስ ከገዢ ፓርቲ ጀምሮ ሌሎች አካላት በመስቀል አደባባይ በተደጋጋሚ ሰልፍ ያደረጉበት መሆኑ እየታወቀ እንደዚህ አይነት ሚዛናዊነት የጎደለው አሰራር መቀበልና በቸልታ ማለፍ ፓርቲያችን ከተመሰረተበት አላማ ጋር የሚጋጭ፣ ከሞራል ፣ከህግና ከፖለቲካ አንጻርም ተቀባይነት የሌለው” አሰራር ነው ብሎአል።

ሰማያዊ ፓርቲ የፊታችን እሁድ በመስቀል አደባባይ የሚያደርገውን የተቃውሞ ሰልፍ እንደማይለውጥ አስታውቋል። ፓርቲው ነሐሴ 26 የጠራው ሰልፍ በጸጥታ ሀይሎች እንዲደናቀፍ መደረጉ ይታወሳል።

አንድነት ፓርቲም በተመሳሳይ መልኩ መስከረም 19 ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ እንደማይችል  እንደተገለጸለት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ ተናግረዋል

የጸጥታ ሀይሎች በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ ሊስትሮዎችን፣ የጎዳና ላይ ነጋዴዎችንና እና በሰልፉ ላይ ይገኛሉ ብሎ የሚጠራጠሩዋቸውን ሰዎች ዛሬም ሲይዙ ውለዋል።

የገዢው ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ዛሬም ድረስ በአገራችን ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳይ ስብሰባ እያደረጉ ነው።