የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች ድርድራቸውን ጀመሩ

ጥር ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰሞኑን ተቋርጦ የነበረው የደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር ዛሬ በጋዝ ላይ የምሽት ክበብ ውስት መጀመሩን ቢቢሲ ዘግቧል። ቀደም ብሎ በሸራተን አዲስ የነበረው የድርድር ቦታ የተቀየረው ቦታውን አትዮጵያን በመጎብኘት ላይ ያሉት የጃፓኑ ጠ/ሚኒስትር ሾኒዝ አቤ በመያዛቸው ነው።

ድርድሩ በምሽት ክለብ ውስጥ መሆኑ አንዳንድ ተደራዳሪዎችን አላስደሰተም። በቤቱ ውስጥ የሚሰማው ጫጫታ እንደረበሻቸው እነዚሁ ልኡካን ገልጸዋል።

ድርድሩ እንደገና ቢጀመርም ዛሬ ከሰአት በሁዋላ ጀበል እየተባለ በሚጠራው የጁባ አካባቢ ከፍተኛ ተኩስ በመሰማቱ ማንኛውም ነዋሪ ከቤት እንዳይወጣ ታዟል። ተኩሱ በዋና ከተማዋ መሰማቱ ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጥሯል። የመንግስት ወታደሮች በነዳጅ ሀብቷ የበለጸገችውን ቤንቲዩን ግዛት መያዛቸውን ማስታወቃቸው ይታወቃል። ተቃዋሚዎች ከከተማዋ ለቀው ቢወጡም በሌላ አቅጣጫ ተኩስ መክፈታቸውም ይሰማል።

የአሜሪካ መንግስት በፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ላይ ጫና እያሳደሩ ሲሆን፣ የዩጋንዳ መንግስት ደግሞ በይፋ መንግስትን እየደገፈ ነው። የተወሰነ አገሪቱ ጦር ጁባ መግባቱም ይናገራል። በአዲስ አበባ የሚካሄደው የሰላም ድርድር ምን ያክል ውጤታማ እንደሚሆን በሚቀጥሉት ቀናት የሚታወቅ ሲሆን፣ የሰላም ድርድሩ ካልሰመ ብዙ ጉዳት ሊደርስ ይችላል ተብሎ ይፈራል።