ሚያዚያ ፲፯ (አስራ ሰባት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የደቡብ ሱዳን መንግስት በአራት የቀድሞ ባለስልጣናት ላይ የከፈተውን የአገር ክዳት ወንጀል እንዲቆምመወሰኑን ተከትሎ፣ ባለስልጣኖቹ ከእስር ቤት ወጥተዋል።
የደህንነት ሚኒስትሩ ኦያይ ደንግ አጃክ፤ የድርጅቱ ዋና ጸሃፈ የነበሩት ፓጋን አሞም፤ የመከላከያ ሚኒስትር ማጀክ ደ አጎት አተም እና በአሜረካ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር የነበሩት እዝቅኤል ሎል ከእስር ቤት ሲወጡ በደጋፊዎቻቸው ከፍተኛ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
መንግስት እርምጃው የተወሰደው ለሰላምና አገሩን ለማረጋጋት ሲባል ብሎአል።
በሬክ ማቻር የሚመራው የደቡብ ሱዳን ተቃዋሚ ቡድን ድርጊቱን በደስታ እንደተቀበለውና ባስቸኳይ የተፈቱት ባለስልጣናት የአዲስ አበባውን ድርድር እንዲቀላቀሉ የሳልቫኪር አስተዳደርን ጠይቋል ::
ከእስር የተፈቱት ባለስልጣናት በበኩላቸው ፣ በፍርድ ቤት ነጻነታቸው ቢረጋገጥ ኖሮ እንደሚመርጡ ተናግረው፣ አላስፈላጊ የሆነው ጦርነት እንዲቆም ጥረት እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።