መጋቢት ፰ (ስምንት)ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የደቡብ ሱዳን መንግስት በቅርቡ የሙርሌ ጎሳ አባላት በጋምቤላ ክልል ጥቃት መፈጸማቸውን ቢያምንም፣ ተወሰዱ ስለተባሉ ህጻናትና ተገደሉ ስለተባሉ ሰዎች ማረጋገጫ አልሰጠም።
የኢህአዴግ ባለስልጣናት ወደ ጁባ በማምራት ከመንግስት ጋር መነጋገራቸውን የገለጸው ራዲዩ ታማዙጂ፣ የቦማ ግዛት አስተዳዳሪዎች ጋምቤላ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ለጁባ መንግስት ቢያስታውቁም አሃዙ ላይ ማረጋገጫ አልሰጡም።
የደቡብ ሱዳን መንግስት በሙርሌ ጎሳ አባላት በኩል የተወሰዱ ህጻናት ካሉ እናሰመልሳለን ያለ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ጦሩዋን ወደ ደቡብ ሱዳን እንድትልክ ፈቃድ አልሰጠም። ጥቃቱን በፈጸሙት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም የሳልቫኪር መንግስት አስታውቛል።
የሙርሌ ጎሳ አባላት 23 ሰዎችን ገድለው 43 ህጻናትን አፍነው መውሰዳቸው መዘገቡ ይታወቃል። ከዚህ በፊት ታፍነው ከተወሰዱት መካከል 80 የሚሆኑት እሳኩን አልተመለሱም።
በጄ/ል ሳሞራ የኑስ የሚመራው የመከላከያ ሰራዊት፣ ከወራት በፊት የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ከእንግዲህ ተመሳሳይ ጥቃት አይፈጸምም በማለት በአደባባይ የዛተ ቢሆንም፣ የሙርሌ ጎሳ አባላት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለ2ኛ ጊዜ ጥቃት ፈጽመዋል።
የደቡብ ሱዳን መንግስት ቀደም ብለው ለተገደሉት ኢትዮጵያውያን ካሳ አልከፈለም።