የኢትዮጵያ የግብርና ዕድገት ወደ 2.5 በመቶ ማሽቆልቆሉ ተገለጸ

ኢሳት (መጋቢት 8 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ ሲመዘገብ የቆየው ሰባት በመቶ የግብርና እድገት በሃገሪቱ ተከስቶ ባለው የድርቅ ምክንያት ወደ 2.5 በመቶ ማሽቆልቆሉ ተገለጸ።

በኢትዮጵያ አራት ክልሎች አዲስ ተከስቶ ባለው ድርቅ ዙሪያ ሃሙስ ለፓርላማ ሪፖርትን ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ፣ ድርቁ በግብርና እድገቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን አብራርተዋል።

በአፋር ኦሮሚያ፣ ደቡብና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ስር በሚገኙ በርካታ ዞኖች ከወራት በፊት በአዲስ መልክ በተከሰተው የድርቅ አደጋ 5.6 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ለአስቸኳይ የምግብ እረዳታ መጋለጣቸው ይታወሳል።

የአለም ባንክን ጨምሮ የተለያዩ አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ድርቁ በሃገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ጫናን በማሳደር ዘርፈ ብዙ ችግር እያስከተለ መሆኑን ሲገልጹ ቆይተዋል። የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ባለፉት ጥቂት አመታት በተከታታይ ሰባት በመቶ እድገትን ሲያስመዘግብ መቆየቱን ያወሱት አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ፣ በቅርቡ በሃገሪቱ በአየር ለውጥ ሳቢያ በተከሰተው የድርቅ አደጋ ዕድገቱ ወደ 2.5 በመቶ ማሽቆልቆሉን ለፓርላማ የስድስት ወር ሪፖርት ባቀረቡ ጊዜ አውስታውቀዋል።

ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርቁ የግብርና ዕድገቱ በከፍተኛ መጠን ማሽቆልቆል ማስመዝገቡን ቢያረጋግጡም በአገር ደረጃ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ተችሏል ሲል ለፓርላማ አባላቱ ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግስታት እና አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች በበኩላቸው በምግብ ዋስትና ራሷን ላልቻለችው የኢትዮጵያ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ የእርዳታ እጁን እንዲዘረጋ እየጠየቁ ይገኛል።

የጀርመኑ ግብረ ሰናይ ድርጅት ሰዎች ለሰዎች 5.6 ሚሊዮን ለሚሆኑ ተረጂዎች አፋጣኝ የምግብ አቅርቦት በአስቸኳይ መድረስ ካልቻለ የሰዎች ህይወት አደጋ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል በቅርቡ ማሳሰቡ ይታወሳል።

በሃገሪቱ ያለው የድርቅ ጉዳይ በቂ አለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን አለማግኘቱን የገለጸው ድርጅቱ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት በከፋ የምግብ እጥረት ሳቢያ የአካልና የጤና ችግር እየደረሰባቸው እንደሆነም አመልክቷል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የኢትዮጵያ መንግስት ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ለተጋለጡ ወደ 6 ሚሊዮን አካባቢ ሰዎችን ለመታደግ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያስፈልግ በጋራ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።

የድርቁ ሁኔታ መባባሱን ተከትሎ ድርጅቱ ከመጠባበቂያ በጀቱ ባለፈው ወር 18 ሚሊዮን ዶላር እንዲሰጥ የወሰነ ሲሆን፣ የተደረገው ልገሳ ተከትሎም መንግስት ከመጠባበቂያ ክምችት እህልን በማውጣት ለተረጂዎች እንዲደርስ ጥረት መጀመሩን አስታውቋል።

ባለፈው አመት በስድስት ክልሎች 10 ሚሊዮን አካባቢ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ለምግብ እርዳታ አጋልጦ የነበረው ተመሳሳይ የድርቅ አደጋ ሙሉ ለሙሉ ሳይቀረፍ አዲስ የድርቅ አደጋ ማጋጠሙ በሰብዓዊ የእርዳታ ስራው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን የእርዳታ ተቋማት ይገልጻሉ።

መንግስት በበኩሉ ድርቁ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አንድ ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቦ ድጋፍ ለመስጠት ጥረት እየተካሄደ እንደሚገኝ አመልክቷል።