ኢትዮጵያ ለተመድ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ፈቃድ እንድትሰጥ ጥያቄ ቀረበ

ኢሳት (መጋቢት 8 ፥ 2009)

የኢትዮጵያ መንግስት ተግባራዊ ተደርጎ በሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ተደርጓል ያለውን ማሻሻያ ተከትሎ ሃገሪቱ ለተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ፈቃድ እንድትሰጥ ተጠየቀ።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የሆነው ሂውማን ራይትስ ዎች፣ የአዋጁ መውጣትን ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል ተፈጽሟል ባለው ግድያና የጅምላ እስራት ላይ ምርመራ ለማካሄድ ጥያቄን አቅርቦ እንደነበር አውስቷል።

ለአዋጁ መውጣት ህዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት እንደሆነ ያስታወቀው ሂውማን ራይስቶ ዎች በዚሁ ተቃውሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ግድያ እና ድብደባ እንዲሁም የጅምላ እስራት እንደተፈጸመባቸው አመልክቷል።

ይህንኑ ድርጊት ተከትሎም የአውሮፓ ህብረት እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጸጥታ ሃይሎች የተፈጸመውን ግድያ በማውገዝ ተወስዷል ያሉት የሃይል ዕርምጃ በገለልተኛ አካል ማጣራትና ምርመራ እንዲካሄድበት ሲጠይቁ ቆይተዋል።

በተያዘው ሳምንት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አፈጻጸም የሚከታተለው ኮማንድ ፖስት አዋጁ ማሻሻያ እንደተደረገበትና ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በመኖሪያ ቤት የሚካሄድ ፍተሻና ብርበራ እንዲቀር ተደርጓል ማለቱ ይታወሳል።

በመገናኛ ብዙሃን እንዲሁም በመንግስታዊ ተቋማት ላይ ከምሽት እስከ ንጋት ድረስ እንቅስቃሴ እንዳይካሄድ ተቀምጦ የነበረውም የአዋጁ ክፍል እንዲቀር መደረጉን የኮማንድ ፖስቱ ሃላፊና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

መንግስት በአዋጁ ላይ ተወስዷል ያለውን ይህንኑ ማሻሻያ ምክንያት በማድረግ ሂውማን ራይትስ ዎች የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት መርማሪ ቡድን ሲያቀርብ ለቆየው ጥያቄ ምላሽን እንዲሰጡ ጠይቋል።

የመርማሪ ቡድኑ በኦሮሚያ ክልል ከተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተጨማሪ ተመሳሳይ የምርመራ ስራን ለማከናወን እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2005 (የምርጫ ሁከት ወቅት) እንዲሁም በ2007, በ2009, 2011 እና በ2015 አም ጥያቄን አቅርቦ እንደነበርና ይሁንታ መንፈጉም ተመልክቷል።

የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ባለፉት በርካታ አመታት አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች የጅምላ እስራት በፖሊስ ጣቢያዎች፣ በወታደራዊ ካምፖችና በማይታወቁ ስፍራዎች ሲያካሄዱ መቆየታቸው በማስረጃ ተደግፎ እንደሚገኝ በሂውማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብት ተመራማሪ የሆኑት ፊሊክስ ሆንር ገልጸዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መውጣት ተከትሎ ብቻ ከ20 ሺ በላይ ለእስር ተዳርገው የነበረ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ከወራት እስራት በኋላ መለቀቃቸው ይታወሳል።

ይሁንና አሁንም ድረስ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ክስ ይመሰረትባቸዋል ተብለው በምርመራ ላይ እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማሻሻያዎች ተደርጎበት እንደሚቀጥል ቢገለጽም እስመቼ ድረስ ቀጣይ እንደሚችል የተሰጠ ዝርዝር መረጃ የለም።