የደራሲ ይስማእከ ወርቁን ሕይወት ለመታደግ ልዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በባሕርዳር ከተማ ሊዘጋጅ ነው
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 16 ቀን 2010 ዓ/ም) ወጣቱ ደራሲና ገጣሚ ይስማእከ ወርቁ ባጋጠመው የመኪና አደጋ ምክንያት የመናገርና የማስታወስ ክህሎቱን አጥቷል። ይህን የአገር ባለውለተኛ በገቢ በማገዝ በውጭ አገር ሕክምናውን እንዲከታተል ለማድረግ በከተማዋ ወጣት የኪነጥበብ አድናቂዎች አማካኝነት እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
አዘጋጆቹ የደራሲው ቀዳሚው ስራ በሆነው ”ዴርቶጋዳ” በተሰኘው መጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሱትን በጣና ሃይቅ ዙሪያ የሚገኙትን ደሴቶችን ጨምሮ፣ የታሪኩ ዋነኛ ስፍራዎችን በጀልባዎች በመዞር ስራዎቹን በመዘከር የገቢ ማሰባሰብ ለማድረግ አቅደዋል። ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር የባህርዳር ከተማ ቅርጫፍ በበኩሉ ከወጣትና አንጋፋ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር የስነጽሑፍ ዝግጅቶችን ለመድረግ ታቅዷል።
ደራሲ ይስማእክ ከአደጋው በኋላ በአዋሳ ሪፈራል ሆስፒታልና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሕክምና ሲደረግለት ቢቆይም፣ በአገር ውስጥ ሕክምና ጤንነቱን ወደ ቀድሞው መመለስ እንደማይቻል ከየሕክምና ቦርዱ የተሰጠው ማረጋገጫ ያሳያል። የ31 ዓመቱን ወጣት ደራሲ ይስማእከ ወርቁን ሕይወት ለመታደግ በሚደረጉ ዝግጅቶች ሁሉም ወገን ተሳታፊ እንዲሆን አዘጋጆቹ ጥሪ አቅርበዋል።