በሽንሌ ዞን የሚካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ አካባቢው በመከላከያ ቁጥጥር ስር እንዲውል ተደረገ

በሽንሌ ዞን የሚካሄደውን ተቃውሞ ተከትሎ አካባቢው በመከላከያ ቁጥጥር ስር እንዲውል ተደረገ
(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 15 ቀን 2010 ዓ/ም) በሽንሌ ዞን ለተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየውን ተቃውሞ ተከትሎ ወታደራዊ እዙ በቀጥታ የሚያዛቸው ወታደሮች አካባቢውን እንዲቆጣጠሩት መደረጉ ታውቋል። በክልሉ መሪ አቶ አብዲ ኢሌ በቀጥታ የሚታዘዙት የልዩ ሃይል አባላት አካባቢውን ተቆጣጥረው የቆዬ ሲሆን፣ እነዚህን ሚሊሺያዎች በመተካት የክልሉ ኮማንድ ፖስት ከዛሬ ጀምሮ አካባቢውን እንደሚቆጣጠረው ለህዝቡ ተናግረዋል።
ለተከታታይ ቀናት በተደረገው ተቃውሞ ወጣቶች እስር ቤቶችን ሰብረው በመግባት እስረኞችን አስፈትተዋል። በአካባቢው የተጀመረውን ተቃውሞ ተከትሎ ባለስልጣናት በመሸሻቸው አብዲ ኢሌና ሌሎች ወታደራዊ አዛዦች ህዝቡ ተቃውሞውን እንዲያቆም ሲማጸኑ ሰንብተዋል። ዘግይቶ በደረሰን ዜና ደግሞ ተቃውሞው ወደ ጅግጅጋ ይሰራጫል በሚል ፍርሃት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የልዩ ሃይል አባላት ጥበቃ እያካሄዱ ነው።
በደጋሃቡር የሚታየው ውጥረት መጨመሩን ተከትሎ ኢንተርኔት እና ኤሌክትሪክ እንዲቋረጥ ተደርጓል። አቶ አብዲ ኢሌ የክልሉን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ ሃኪም ኢጋልን ለማባረር ያደረገውን ሙከራ ተከትሎ በሶህዴፓ ፓርቲ ውስጥ ውጥረት መስፈኑንም ምንጮች ገልጸዋል።