(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 26/2011) በታጣቂዎች ታፍነው የተወሰዱትን የደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንትን ለማስመለስ ሁሉንም አማራጮች እየተጠቀመ መሆኑን ኦዴፓ አስታወቀ።
የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ ለኢሳት እንደገለጹት የደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳላሳ ቡልቻ በታጣቂዎች ታፍነው ከተወሰዱበት ጊዜ አንስቶ የክልሉ መንግስት ማንኛውንም መንገድ በመጠቀም ለማስመለስ እየተንቀሳቀሰ ነው።
በሌላ በኩል በምዕራብ ጉጂ ዞን ገላን ወረዳ ታፍነው የተወሰዱትን ሶስት አመራሮች በተመለከተ በአካባቢው ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን ኦዴፓ አስታውቋል።
ዶክተር ዳለሳ ቡልቻ ከደንቢዶሎ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ እያሉ ነው ረቡዕ ዕለት በታጣቂዎች ታፍነው የተወሰዱት።
የደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳላሳ ቡልቻ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተደጋጋሚ ዛቻ ይደርሳቸው ነበር።
የግድያ ማስፈራሪያ ተልኮላቸዋል። ከአንድ ወር በፊት የመኖር ስጋት እንደገጠማቸው በመጥቀስ ለሚመለከተው የመንግስት አካል ሁኔታውን አሳውቀውም ነበር።
ይህን የተረዳው የአቶ ለማ መገርሳ ክልላዊ መንግስት የግድያ ዛቻ የደረሰባቸውን ዶክተር ዳላሳን ወደ አዲስ አበባ እንዲዛወሩ በማድረግ የኦሮሚያ ክልል ውሃ ቢሮ ምክትል ሃላፊ እንዲሆኑ ሹመት ይሰጣቸዋል።
ዶክተር ዳላሳ ግን ከደምቢዶሎ መንቀሳቀስ አልቻሉም። እስከአዲስ አበባ የተዘረጋው መስመር በመዘጋቱና ከፍተኛ የደህንነት ስጋት የተደቀነበት በመሆኑ ባሉበት ደምቢዶሎ ቀሩ።
ከሁለት ሳምንት ወዲህ ግን አንጻራዊ ሰላም መስፈኑንና መከላከያ ሰራዊትም ወደ አካባቢው መሰማራቱን ተከትሎ ዶክተር ዳላሳ ቡልቻ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ይጀመራሉ።
ረቡዕ ዕለት እሳቸውን ያሳፈረችው ተሽከርካሪ ከደምቢዶሎ ብትነሳም የቄሌም ወለጋዋን ጋባ ሮቢ መንደርን ማለፍ አልቻለችም።
ድንገት በታጣቂዎች ተከበበች። የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳላሳ ከሹፌራቸው ጋር ታፍነው ተወሰዱ።
የታጣቂዎቹን ማንነት በተመለከተ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ባለስልጣናት የተሰጠ መረጃ የለም።
የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ቢሮ ሃላፊው አቶ አዲሱ አረጋ በግል ፌስቡክ ገጻቸው የዶክተር ዳላሳን መታፈን ይፋ አድርገዋል።
ኢሳት ያነጋገራቸው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ታዬ ደንደአ የዶክተር ዳላሳን ታፍኖ መወሰድ አረጋግጠዋል።
ኦዴፓ ከመንግስት ጋር በመሆን ዶክተር ዳላሳን ለማስመለስ የትኛውንም አማራጭ ተጠቅሞ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነም አቶ ታዬ ገልጸዋል።
አቶ ታዬ ታጣቂዎቹ ዶክተር ገላሳን የወሰዱበት ቦታ ለጊዜው ባይታወቅም የተለያዩ አማራጮችን ይዘን እያሰስን ነው ብለዋል።
የክልሉም ሆነ የኦዴፓ ባለስልጣናት በዶክተር ዳላሳ ቡልቻ አፈና ላይ የተሰማሩትን ታጣቂዎች በስም መግለጽ ባይፈልጉም የኦነግ ታጣቂዎች መሆናቸውን የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ያረጋግጣሉ።
ኦነግ በምዕራብና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች አስተዳዳሪዎችን ጭምር መግደሉን የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ይፋ አድርገዋል።
በምዕራብ ጉጂ ባለፈው ሳምንት በኦነግ ታጣቂዎች ታፍነው ስለተወሰዱ የገላን ወረዳ አመራሮችን በተመለከተ የተጠየቁት አቶ ታዬ ደንደአ በዚያ አካባቢ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ ሊያመጣ በሚችል መልኩ መንግስት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።
3ቱ አመራሮችን ለማስፈታት በአባገዳዎች ሽምግልና የተጀመረ ቢሆንም እስከአሁን ሊለቀቁ እንዳልቻሉ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በሌላ በኩል ታዋቂው አክቲቪስት ገረሱ ቱፋ የአሜሪካን ፓስፖርት ባለውና ስሙን ባልገለጸው ግለሰብ በተደራጁ ወጣቶች እሱንና የተወሰኑ አክቲቪስቶችን ለመግደል እቅድ እንዳላቸው ገለጿል።
አክቲቪስት ገረሱ በግል ገጹ ላይ እንዳሰፈረው አምቦ ከሄድን እንድንገደል ዝርዝር ውስጥ ከተጠቀሱት የሱ ስም ይገኝበታል።
ይህን በገንዘብ የሚደግፈውንና የአሜሪካን ፓስፖርት አለው ያለውን ግለሰብ ማንነት ግን አልገለጸም።