የየመን አማጽያን ኤደንን ለመያዝ መቃረባቸው ተሰማ

የየመንን ዋና ከተማ ሰንአን በመቆጣጠር ሁለተኛዋን ታላቋን ከተማ ኤደንን ለመቆጣጠር ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በመፋለም ላይ የሚገኙት የሃውቲ ሚሊሺያዎች፣ ከሳውድ አረቢያ የሚደርስባቸውን የአየር ጥቃት ተቋቁመው ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር መቃረባቸውን መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው።

አማጽያኑ በሚደርስባቸው የአየር ጥቃት ሳይበገሩ፣ የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ታማኝ ወታደሮች በመፋለም ላይ ናቸው።አሜሪካ ለሳውድ አረቢያ ወታደራዊ ቁሳቁሶችን በማቅረብ ላይ መሆኗን ገልጻለች። ኢራን በበኩሉዋ ተዋጊ መርከቦቿን ወደ አካባቢው ልካለች።

በየመን የሚገኘው ጦርነት እየተባባሰ መሄዱን ተከትሎ በአገሪቱ የሚገኙ የውጭ አገር ዜጎች ሁኔታ አሁንም አሳሳቢ ሆኖ እንደቀጠለ ነው። እስካሁን  ዜጓቿን ከየመን በአየር በማስወጣት የተሳካ ስራ በመስራት ላይ የምትገኘው ህንድ ናት። በየመን የሚኖሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ህንዶች ባለፉት ሁለት ቀናት ከአገሪቱ ወጥተዋል።

የኢትዮጵያውያን ሁኔታ አሁን አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል። አለማፍ የስደተኞች ድርጅት በሚቀጥሉት ቀናት በሺዎች የሚቆጠሩ የውጭ አገር ዜጎችን እንደሚያስወጣ ገልጿል።