አቶ ኤርጫፎ ኤርዴሎ ለምርጫ ቅስቀሳ በሄዱበት ከፍተኛ ጫና እንደደረሳበቸው አስታወቁ

መጋቢት ፴(ሠላሳ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በ9 ፓርቲዎች ትብብር ስር የሚንቀሳቀሰው የከምባታ ህዝቦች ኮንግረስ  ሊ/መንበር አቶ ኤርጫፎ ኤርዴሎ የምርጫ ቅስቀሳ ለማድረግ ወደ ትውልድ ቀያቸው አንገቻ ወረዳ ቢያቀኑም፣ የወረዳው አመራሮች ከፍተኛ ችግር እንደፈጠሩባቸው ለኢሳት ተናግረዋል።

ወደ ወረዳው በመሄድ የምርጫ ፖስተሮችን ሲለጥፉ እንደተቀደደባቸው፣ የተከራዩትን ቤት እንዲለቁ መገደዳቸውን የገለጹት አቶ ኤርጫፎ ይባስ ብሎ ከተማው ውስጥ ሆቴል ለመያዝ ሲጠይቁ፣ ባለሆቴሎቹ “አታከራዩ” ተብለናል በሚል እንደከለከሉዋቸው ገልጸዋል።

ከተማ ውስጥ ማረፊያ በማጣታቸው ገጠር ከዘመዶቻቸው ጋር ለመቀመጥ መገደዳቸውንም አቶ ኤርጫፎ ተናግረዋል

በሌላ በኩል ደግሞ የመድረክ እጩ ተወዳዳሪዎች በአዋጅ የተሰጠንን መብት እንዳንጠቀም ተከለከልን፤በየቦታው በመንግስት ሃላፊዎችና ታጣቂዎች እየተንገላታን ነው ብለዋል።

በኦሮሚያ አስተዳደር አርጡማ ፉርሲ ወረዳ የምርጫ ክልልን በመወከል ለፓርላማ የሚወዳደሩት መምህር ታደሰ ወርቁ ለዘጋቢያችን እንደገለጹት የምረጡኝ ቅስቀሳ ለማድረግ የሚያስችላቸውን መብት ለመጠቀም አለመቻላቸውን ተናግረዋል።

በምርጫ ደንቡ 171/2002 አንቀጽ 44 ለ እና ሐ በተደነገገው መሰረት ፈቃድ በመጠየቅ የቅስቀሳ ስራችን ለመስራት በምንሞክርበት ጊዜ ደንቡን እያወቁ የስራ ሃላፊዎች ፈቃድ በመከልከል ተጽዕኖ እንደሚያደረሱባቸው ተናግረዋል፡፡

ህዝቡን ለመቀስቀስ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ከተራ ፖሊስ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ መኮንኖች ያሉ የመንግስት አቀንቃኞች በማንገላታት ችግር  እያደረሱባቸው መሆኑን የገለጹት መምህሩ፤የምርጫ ቅስቀሳ ወረቀት ለህብረተሰቡ በሚሰጡበት ጊዜ በህዝብ ፊት ማዋረድ፣  የማይገባ ስድብ መስደብና ከፖሊስ መኮንኖች የማይጠበቅ ድርጊት በመፈጸም  በየቦታው ችግር  እያደረሱባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ ባለው ደካማ አሰራር የተነሳ በርካታ የገዢው ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች በአስመራጭነት ተመድበው መስራታቸውን ብናስታውቅም፣ ቦርዱ ተከታትሎ እርምጃ ባለመውሰዱ የምርጫውን ተአማኒነት አደጋ ላይ ጥሎታል ብለዋል።