የዘንድሮው ምርጫ ለኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን ለተቃዋሚዎችም መልእክት ያስተላለፈ ነበር ተባለ

ሚያዚያ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- ህዝቡ በዘንድሮው የአካባቢና የወረዳ ምርጫ ህዝቡ ኢህአዴግን ለመቃወም እንደተጠቀመበት ከተለያዩ አካባቢዎች ያሰባሰብናቸው መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን፣ መልእከቶቹ ግን ለኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚዎችም የህዝቡን ጥያቄ እንዲሰሙ የሚያመለክቱ መሆናቸውን ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች እና አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።

በደቡብ ኦሞ ዞን የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ህብረት የዞኑ ሰብሳቢ የሆኑት መምህር አለማየሁ መኮንን ለኢሳት እንደገለጡት በዞናቸው የተካሄደው ምርጫ ህዝቡ በአገዛዙ ላይ ያለውን ተቃውሞ ከመግለጽ ባሻገር ተቃዋሚዎችም ህዝቡን ለለውጥ እንዲያነሳሱ ጥሪ የሚያቀርብ ነው።

መምህር አለማየሁ ተቃዋሚ ድርጅቶች ህዝቡን በማስተባበር  ሰላማዊ ተቃውሞ እንዳላደረጉ ገልጸው፣ ህዝቡን ማስተባበር ዛሬ ግድ ይላል ብለዋል ።

የአንድነት ፓርቲ የደቡብ ኦሞ ዞን ተወካይ አቶ ስለሺ ጌታቸው በተመሳሳይ መንገድ እንደገለጹት ምርጫው ለተቃዋሚዎችም መልእክት አስተላልፏል።

አንድ አባት ተቃዋሚዎች ወደ ፊት እንዲወጡ እና ህዝቡን እንዲያስተባባሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ህዝቡ የሚያቀርባቸውን አስተያየቶች በ ከእርስዎ ለርሶ  ዝግጅት መከታተል የምትችሉ መሆኑን ለማስታወስ እንወዳለን።