ሲአን አባሎቹ እንደታሰሩበት አስታወቀ

ሚያዚያ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- ለሲዳማ ህዝብ አስተዳደራዊ መብቶች የሚታገለው ሲአን ለኢሳት እንደገለጸው ከዘንድሮው ምርጫ ራሱን ካገለለ በሁዋላ በገዢው ፓርቲ የሚደርስበት ወከባ ተጠናክሮ ቀጥሎአል።

ድርጅቱ እንደገለጸው በትናንትናው እለት አራት አባሎቹ በቡርሳ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርበው በእስራት እንዲቀጡ ተፈርዶባቸዋል። አቶ ወገሳ ጭቆ በአራት ወራት እስራትና 500 ብር ፣ አቶ ለገሰ ለቀሙ በስድስት ወራት እስራትና 500 ብር፣ አቶ ወሸራ አጋላ፣ በ6 ወርና 500 ብር፣ አቶ በቀለ ጁባ አንድ አመት ከስድስት ወራት ተፈርዶባቸዋል። እስረኞቹ በአሁኑ ጊዜ በይርጋለም እስር ቤት ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ ታውቋል።

በቡርሳ ወረዳ ታስረው ከሚገኙት የድርጅቱ አባሎች መካከል ደግሞ   አቶ ደምሴ ዳጣ፣ ለማ ቡቃሳ፣  ታደሴ ወሼ፣ ሾሜ ወጋርሳ፣ ሸለሞ ቦጋ፣ ቆቃ ያዲቴ፣ አየላ አሩሳ፣ ኑረዲን ማቀቦ፣ ብርሀኑ ክፍሌ ፣ ተስፋየ ታምሩ እና በቀለ ቦጋኖ ይጠቀሳሉ።

ሌሎች የድርጅቱ አባሎችም እንዲሁ ወደ ተለያዩ ቦታዎች ተሰደው እንደሚገኙ ድርጅቱ አስታውቋል።

በጉዳዩ ዙሪያ የክልሉን መንግስትን ባለስልጣናት ለማነጋገር  ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።