የዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን ባለፈው ቅዳሜ በመንግሥታዊ ድርጅቶች አስተባባሪነት ሲከበር በኢትዮጽያ ስላለው የፕሬስ አፈናና ስለታሰሩ ጋዜጠኞች ጉዳይ ምንም ሳይወያይ ተበተነ፡፡

ሚያዚያ ፳፯ (ሃያ ሰባት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በየዓመቱ ሜይ 3 ቀን የሚከበረው የዓለም የፕሬስ ቀን በኢትዮጽያ ለአምስተኛ ጊዜ ባለፈው ቅዳሜ በግዮን ሆቴል የተከበረ ሲሆን የስብሰባው አዘጋጅ ሆነው የተገኙት የመንግስት ኮምኒኬሽን ጽ/ቤት እና የአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ ናቸው፡፡ ቀኑ የፕሬስ ነጻነት የሚታሰብበትና ጋዜጠኞች በስራዎቻቸው ዙሪያ ስለገጠማቸው ችግሮች የሚወያዩበት ቢሆንም በመንግስታዊ ድርጅቶቹ ተጠልፎ ስለፕሬስ ካውንስል ምስረታ ጉዳይ ሪፖርት ሲቀርብበት መዋሉ አሳዛኝ መሆኑን ስብሰባውን የተከታተሉ ወገኖች ተናግረዋል፡፡

የመንግስት ኮምኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን በመድረኩ ላይ ተገኝተው ሕግና ስርዓት አይከተሉም ያሉዋቸውን ፕሬሶች ካብጠለጠሉ በሁዋላ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው የሚያስጠነቅቅ ንግግር አድርገዋል፡፡ ይህ የአቶ ሬድዋን ንግግር መንግስት ቀጣዩን ምርጫ መሰረት አድርጎ የነጻውን ፕሬስ ለመዝጋትና ለማዳከም ያለውን ዝግጅት ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው ተብሎአል፡፡

በበዓሉ ላይ የተገኙት አብዛኛዎቹ የኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ፕሬሱ ለመንግስትና ለሕዝብ የሚጠቅም ስራ እያከናወነ አይደለም፣ ሽብር የሚያፋፍምና ብሔርና ከብሔር የሚያጋጩ ዘገባዎችን ያቀርባል በሚል መንግስት እርምጃ እንዲወስድ ሲወተውቱ ተደምጠዋል፡፡

በተለይ ሰሞኑን 3 ያህል ጋዜጠኞችና 6 ብሎገሮች ዞን 9 በመባል የሚታወቅ ቡድን መስርተዋል በሚል በደህንነት ሃይሎች ተይዘው ዘብጥያ በወረዱበት ሰሞን፣  ይህንን አጀንዳ ምንም ሳያነሱ የዓለም የፕሬስ ቀን ማክበር አሳዛኝ መሆኑን የጠቀሱት ምንጮቻችን ፣ መድረኩ ነጻ አይደለም በማለት አብዛኛው የነጻ ፕሬስ አባላት ሳይገኙ መቅረታቸው ታውቋል፡፡