(ኢሳት ዲሲ–ጥር 3/2010)
ኢትዮጵያ ሕጻናትን በጉዲፈቻ ወደ ውጭ ለመውሰድ የሚፈቅደውን ሕግ በፓርላማ በኩል አገደች።
ሕጉ የታገደው በጉዲፈቻ ስም በውጭ ዜጎች ከኢትዮጵያ የሚወሰዱ ሕጻናት ለበርካታ ጊዜያት በአሳዳጊዎቻቸው ከፍተኛ በደል እንደሚደርስባቸው በመታወቁ ነው ተብሏል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በጉዲፈቻ መልክ ከኢትዮጵያ የሚወሰዱ ሕጻናት ብዙዎቹ ደብዛቸው ሲጠፋ አንዳንዶቹ ደግሞ እስከመገደል ደርሰዋል።
ሕጻናትን በጉዲፈቻ ለማሳደግ በሚል ከኢትዮጵያ በርካታ ልጆች ከሀገር እንዲወጡ ተደርጓል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1999 ወዲህ ብቻ 15 ሺ ሕጻናት በጉዲፈቻ መልክ ወደ አሜሪካ መወሰዳቸው ነው የሚታወቀው።
ሕጻናቱ በዚህ መልክ ከሀገር ከወጡ በኋላ ግን ደህንነታቸው በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ እንደማይታወቅ ነው የሚነገረው።
ብዙዎቹ በአሳዳጊዎቻቸው ከፍተኛ በደልና እንግልት እንደሚደርስባቸው ሲገለጽ ቆይቷል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013 ሁለት አሜሪካውያን ባልና ሚስቶች አንዲት ኢትዮጵያዊ ለማሳደግ ከወሰዱ በኋላ ገድለዋት በመገኘታቸው በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳዩ ሲያነጋግር እንደነበር አይዘነጋም።
በአሜሪካውያኑ ላይ ከፍተኛ የእስራት ጊዜ ቢፈረድባቸውም በተመሳሳይ ሁኔታ የተጎዱ ኢትዮጵያውያን ስለመኖራቸው ግን እንደ አንድ ማሳያ ታይቶ ነበር።
እናም ሕጻናቱ በህገወጥ የሰው ንግድ በተሰማሩ ሰዎች ለአደጋ መጋለጣቸው በዙዎቹን ዜጎች ሲያሳስብ ነው የቆየው።
በዚሁም ምክንያት የኢትዮጵያ ፓርላማ ጉዳዩን ትኩረት በመስጠት በመጨረሻ ሕጻናትን በጉዲፈቻ መልክ ወደ ውጭ ለመውሰድ የሚፈቅደውን ሕግ ሙሉ በሙሉ አግዶታል ብሏል ቢቢሲ በዘገባው።
ፓርላማው ለተለያዩ ችግሮች የተጋለጡ ሕጻናት በሀገር ውስጥ የሚረዱበት ሁኔታ እንደሚመቻችም ገልጿል።
ይህም በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ሊከናወን ይችላል ተብሏል።
ጉዲፈቻ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሆነ ግን ክልከላ እንደማይደረግበት ነው የተገለጸው።