የውጭ ምንዛሬ እጥረት በእህልና በእቃዎች ዋጋ ላይ ጭማሪ እያስከተለ ነው

የካቲት ፲፫ (አስራ ሶስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በኢትዮጵያ የተከሰተው አሳሳቢ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ነዳጅን ጨምሮ በተለያዩ ከውጭ ተገዝተው በሚመጡ እቃዎች እና በእህል ዋጋ ላይ ጭማሪ እያሳየ መምጣቱ ታወቀ

ዘጋቢያችን እንደገለጠው ካለፉት 7 ወራት ጀምሮ የተከሰተው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ ከውጭ በሚገቡ በተለይም ከትራንስፖርት ጋራ ተያያዢነት ባላቸው እቃዎች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ ነው።

የፍጆታ እቃዎች ባልሆኑት ላይ የታየው ጭማሪ በእህል ዋጋ ላይም ጭማሪ እንዲከሰት እያደረገው ነው። ባለፈው ጥቅምት ወር ወደ አንድ አሀዝ ይወርዳል ተብሎ የተገመተው የዋጋ ንረት ፣ ላለፉት ሶስት ወራት መጠነኛ መረጋጋት ያሳየ ቢሆንም ተመልሶ እየጨመረ መምጣቱን ህብረተሰቡን እያማረረ ነው።

በመላው አገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ጊዜ ቁጥር እንድ ችግር ብለው የሚወስዱት የኑሮ ውድነቱ መሆኑን መንግስት ባለፈው ሳምንትየተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አነጋገሮ ካሰባሰበው መረጃ ለማወቅ ተችሎአል።

በመንግስት መረጃ መሰረት በእየለቱ የሚጎነውን የኑሮ ውድነት መግታት ካልተቻለ፣ ህብረተሰቡ እስከ ዛሬ የታገሰውን ያክል ላይ ላይታገስ  ይችላል።

ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ የመጣውን የእህል ዋጋ ለማረጋጋት መንግስት ተጨማሪ ስንዴ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ እያስገባ ነው። በቅርቡ ከገባው 500 ሺ ኩንታል ስንዴ በተጨማሪ ወደ 4 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ እህል ተገዝቷል።

ሪፖርተር ዛሬ እንደዘገበው ደግሞ መንግሥት በተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት እስከ ሰኔ ወር ድረስ ለኢንዱስትሪዎችና ለዘመናዊ እርሻዎች ብቻ ቅድሚያ እንዲሰጥ ወስኗል።

የንግዱ ማኅበረተሰብ በርካታ የውጭ ምንዛሪ ጥያቄዎችን ለባንኮች ሲያቀርቡ ቢሰነብቱም፣ በተፈጠረ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ሊስተናገዱ አልቻለም፡፡ ጉዳዩን በሚመለከት መንግሥት የተከሰተው ሰው ሠራሽ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው የሚል መግለጫ ሲሰጥ ቢቆይም፣ በተካሄዱ ተደጋጋሚ የፋይናንስ ዘርፍ ግምገማዎች መንግሥት የውጭ ምንዛሪ እጥረት መኖሩን ለማመን ተገዷል።

መንግሥት በጊዜያዊነት የውጭ ምንዛሪ ቅድሚያ ለኢንዱስትሪው ዘርፍና የዘመናዊ እርሻ አካል ለሆኑት የአበባና የአትክልት እርሻዎች ብቻ እንዲሰጥ ወስኗል፡፡

የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት በአንድ ዶላር እስከ 1.70 ብር በጉቦ መልክ መስጠት የተለመደ መሆኑን፣ ብሄራዊ ባንክም እርምጃ እንደሚወሰድ እያስጠነቀቀ መሆኑን ጋዜጣው ዘግቧል።