ዜና (የካቲት 2 ፥ 2009)
ባለፉት ስድስት ወራቶች ኢትዮጵያን ከጎበኙ የውጭ ሃገር ቱሪስቶች የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ በ145 ሚሊዮን ዶላር (በ3 ቢሊዮን ብር) አካባቢ መቀነሱን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሃሙስ አስታወቀ።
በኦሮሚያ ክልል ለአንድ አመት ያህል የዘለቀውና በሃምሌ ወር 2008 አም በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ በቱሪዝም ገቢው እንዲቀንስ አስተዋጽዖ ማድረጉን ሚኒስቴሩ አክሎ ገልጿል።
በሃገሪቱ የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመቆጣጠር ሲባል በትቅምት ወር ተግባራዊ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የቱሪስቶች ቁጥር እንዲቀንስ ማድረጉም ታውቋል።
የአዋጁ መውጣትን ተከትሎ የአሜሪካ፣ ብሪታኒያ እና የተለያዩ የአውሮፓ ሃገራት ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይጓዙ እገዳን ጥለው የነበረ ሲሆን ዕርምጃው በኢትዮጵያ የቱሪዝም ገቢ ላይ ተፅዕኖ አድርጎ መቆየቱን ለመረዳት ተችሏል።
የስድስት ወር የስራ አፈጻጸሙን አስመልክቶ ሪፖርቱን ያቀረበው ሚኒስትሩ በተያዘው ግማሽ አመት ሃገሪቱን ከጎበኙ 439 ሺ አካባቢ ቱሪስቶች ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ሊገኝ መቻሉን አመልክቷል።
ይሁንና በስድስት ወራቶች ውስጥ የተገኘው ገቢ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ145 ሚሊዮን ዶላር (በሶስት ቢሊዮን ብር አካባቢ) ቀንሶ መገኘቱን የሚኒስቴሩ ቀል አቀባይ አቶ ገዛኸኝ አባት ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
ባለፉት ስድስት ወራቶች የቱሪስቶች ቁጥር ደግሞ በ40ሺ አካባቢ መቀነሱ ታውቋል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በተያዘው በጀት አመት ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ቱሪስቶች ሃገሪቱን ይጎበኛሉ ብሎ እቅድን የነደፉ ሲሆን፣ ለስድስት ወር ይቆያል የተባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በእቅዱ ላይ ጫና ማሳደሩን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ። አዋጁ አሁም ድረስ ባለመነሳቱ ወደ ሃገሪቱ የሚጓዙ የቱሪስቶች ቁጥር መጨመር ሊያሳይ አለመቻሉን አስጎብኚ ድርጅቶች አስታውቀዋል።
ከቱሪስት የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ መቀነስ በሃገሪቱ የኢኮኖሚ እና የውጭ ምንዛሪ ክምችት ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖን እንደሚያሳደር የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ገልጸዋል።
ከቱሪስት ዘርፉ በተጨማሪ የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ ገቢ ማስቆልቆል ለሃገሪቱ ፈታኝ ሆኖ መቀጠሉን የመንግስት ባለስልጣናት በቅርቡ ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።
ጠ/ሚ/ር ሃይለማሪያም ደሳለኝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በቱሪስቶች እንቅስቃሴና ገቢ ላይ ተፅዕኖ አላደረገም በማለት በቅርቡ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል።