ሰኔ ፲(አስር)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በሃረር በቅርቡ ከተነሳው ቃጠሎ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ ከሚገኙት ከ20 በላይ ነጋዴዎችና ሰራተኞች መካከል ፍርድ ቤት የቀረቡት 3ቱ ተከሳሾች እንደገና ሌላ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል።
የ25 አመቱ ቢኒያም ጌታቸው፣ የ28 አመቱ ሲሳይ አሊ አህመድ እና የ16 አመቱ ዙቤር አህመድ በ1996 ዓም የወጣውን የወንጀል ህግ በመተላለፍ ” በፌደራል ህገመንግስት የተቋቋመውን የሃረሪ ህዝብ ክልል መንግስት ፣ በዚህ ክልል መንግስት የተቋቋሙትን የአስፈጻሚ አካላትን የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኞች መስሪያ ቤቱ የእለት ተእለት ስራውን በተለይም የትራንስፖርት መገናኛ ጽ/ቤት ባለስልጣን እና ሰራተኞች እንዲሁም የክልሉ ፖሊስ ሃይል አባላት የሃረር ብሀረሰብ እና ሰራተኞች በፌደራልና በክልል ህገመንግስት የተሰጣቸውን የማስተዳደር ስልጣን ለማደናቀፍ ተከሳሾች መጋቢት 1/2006 ዓም ከጠዋቱ ከ3፡00 እስከ 7 ሰአት ባለው ጊዜ በቀበሌ 14 ውስጥ በሚገኘው የትራንስፖርትና መገናኛ ጽ/ቤት እና ፊት ለፊቱ ባለው መንገድ ከ300 እስከ 500 የሚሆኑ ህወገወጥ ስለፈኞችን በመምራት በዛቻ፣ መንገድ በመዝጋት፣ ድንጋይ በመወርወር የመንግስት ሰራተኞች እና የክልሉ ነዋሪዎች ወደ እለት ስራዎች እንዳይሄዱ በመከላከል በመንገድ ትራንስፖርት መገናኛ ጽ/ቤት ላይ ግምቱ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ እና እንዲደርስ በማድረግ፣ አንድን ብሄረሰብ ነጥሎና ፖሊስን በመሳደብ፣ የመንገድ ትራንስፖርት መገናኛ ጽ/ቤት በእሳት ለማጋየት በሞመከር የክልሉን ሰንደቃላማ ከተሰቀለበት በማውረድ የመንግስትና የህዝብ ንብረት በማውደም የክልሉን ህገመንግስታዊ ተግባርን በማደናቀፍ ወንጀል” መከሰሳቸውን የክስ ቻርጁ ያመለክታል።
በተለይ አንደኛው ተከሳሽ ቢኒያም ጌታቸው የሃረሪ ክልልን ሰንደቃላማ በንቀት ከተሰቀለበት በማውረድና በማቃጠሉ የመንግስት ምልክት በመድፈር ወንጀል መከሰሱን የክስ ጃርጁ ያመለክታል።
ሶስቱም ተከሳሾች ” የሃረሪ ክልል ባለስልጣኖችን፣ ያሃረሪ ፖሊስን፣ የሃረሪ ብሄረሰብን ሌባ በማለት የሃሰት ወሬዎችን በመንዛት የፖለቲካና የዘር ጥላቻን በመቀስቀስ በፈጸሙት የሃሰት ወሬዎችን በማውራት ህዝብን በማነሳሳት ወንጀል መከሰሳቸውንም የክስ ቻርጁ ይዘረዝራል። ተከሳሾች በበኩላቸው የሃረሪን መንግስት እንጅ ህዝቡን አልተሳደብንም በሚል እየተከራከሩ ነው።
ፍርድ ቤቱ የዳኛ እጥረት አለብን በሚል ለሃምሌ 24 ቀጠሮ ሰጥቷል። በ20 ሰራተኞችና ነጋዴዎች ላይ የተመሰረተው ክስ ደግሞ ሰኔ 20 ቀን እንደሚታይ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።