(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 3/2010)በአሸባሪነት ተከሰው ከአመት በላይ በወህኒ ቤት የሚገኙት የዋልድባ መነኮሳት ክሳቸው ተቋርጦ እንዲፈቱ መወሰኑን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።
ሁለቱን የዋልድባ መነኮሳት ጨምሮ 114 ሰዎች ክሳቸው እንዲቋረጥ የተወሰነ ሲሆን ይህም መንግስት እስረኞችን ለመልቀቅ ያሳለፈው ውሳኔ አካል እንደሆነም ተመልክቷል።
ከዋልድባ አበረንታ ገዳም በምንኩስና ይኖሩ የነበሩትና የዋልድባ ገዳም መታረሱን በመቃወማቸው ሲፈለጉ ቆይተው ከአመት በፊት ወደ ወህኒ የተጋዙት አባ ገብረኢየሱስ ኪዳነማርያም ከሌላው መነኩሴ አባ ገብረስላሴ ወልደሃይማኖት ጋር በአሸባሪነት ተከሰው በወህኒ ቤት ቆይተዋል።
የሕሊናና የፖለቲካ እስረኞች በጥር መጨረሻ እንዲሁም በየካቲት መጀመሪያ በተፈቱበት ወቅት ይለቀቃሉ ተብለው ከተጠበቁት ውስጥ የዋልድባ መነኮሳትም ይገኙበታል።ሆኖም ክሳቸው ቀጥሎ በፍርድ ሲመላለሱ ቆይተዋል።
ሌሎቹ ከተፈቱ ከ2 ወር በኋላ ክሳቸው መቋረጡ ይፋ ሆኗል።
በእነ ተሻገር ወልደሚካኤል የክስ መዝገብ የአሸባሪነት ክስ ተመስርቶባቸው በወህኒ ቤት የቆዩት ሁለቱ መነኮሳት ክሳቸው መቋረጡን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ቢያሳውቅም የሚፈቱበት ቀን ግን በግልጽ አልተነገረም።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በቅርቡ በይቅርታ የተፈቱ ሰዎች ተመልሰው በመታሰር ላይ መሆናቸውም ተመልክቷል።
ከቂሊንጦና ቃሊቲ ወህኒ ቤት ከወር በፊት በይቅርታ የተፈቱ ሁለት የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪዎች በድጋሚ የታሰሩት ትላንት እንደሆነም ታውቋል።
ባንተወሰን አበበና መርከዲዮስ ሽብሩ የተባሉትና በቅርቡ በይቅርታ የተፈቱት ሁለቱ ወጣቶች ትላንት ረቡዕ ሚያዚያ 2/2010 አርባምንጭ ከተማ ውስጥ ተይዘው በከተማዋ ዳርቻ በሚገኝ ወህኒ ቤት መታሰራቸው ተመልክቷል።
መንግስት የፖለቲካ እስረኞችን ለመፍታት መወሰኑን ተከትሎ ታዋቂ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች እንዲሁም የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በከፊል የተፈቱ ቢሆንም ታዋቂውን ፖለቲከኛ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች አሁንም በወህኒ ቤት ይገኛሉ።
መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤን ጨምሮ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ባልደረቦችና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ዛሬም እንዳልተፈቱ ታውቋል።