አንድ የአልጄሪያ ወታደራዊ አውሮፕላን ተከሰከሰ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 3/2010) አንድ የአልጄሪያ ወታደራዊ አውሮፕላን ተከሰከሰ።

በአደጋው የአውሮፕላኑን ሰራተኞች ጨምሮ 257 ሰዎች አልቀዋል።

ዛሬ ረቡዕ ማለዳ  ከአልጄሪያ ርዕሰ መዲና አልጀርስ ወጣ  ብሎ የተከሰከሰው ይህ  ወታደራዊ አውሮፕላን በአብዛኛው ያሳፈረው ወታደሮችን ሲሆን ወደ ሌላ የአልጄሪያ ግዛት በመጓዝ ላይ እያለ በተነሳ በአጭር ግዜ ውስጥ መከስከሱም ተመልክቷል።

የአልጄሪያ መንግስታዊ ቴሊቪዥን የሃገሪቱን መከላከያ ሚኒስቴር ጠቅሶ እንደዘገበው  247 መንገደኞችንና 10 የአውሮፕላኑን ሰራተኞች የያዘው አውሮፕላን ቡፋሪቅ ከተባለው የሃገሪቱ ወታደራዊ አውሮፕላን ማረፊያ  እንደተነሳ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ዛሬ ረቡዕ ማለዳ ተከስክሷል።

ጉዞው ወደ ሃገሪቱ ምዕራባዊ ከተማ በቻር እንደነበርም ተመልክቷል።

ኢሉዥን አንድ አይ 176 የተባለው ሩሲያ ስሪት አውሮፕላን ካሳፈራቸው 247 መንገደኞች 26 ቱ የፖሊሳሪዮ ግንባር አባላት እንደሆኑም ተዘግቧል።

ፖሊሳሪዮ ከሞሮኮ ለመገንጠል የሚንቀሳቀሰው የምዕራብ ሰሃራ ሪፐብሊክ ነጻ አውጪ ሰራዊት መሆኑም ይታወቃል።

ይህ አደጋ አልጄሪያ ከ 15 ዓመታት ወዲህ የገጠማት ከፍተኛ አደጋ እንደሆነም ታውቋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ 2003 የሃገሪቱ የመንገደኞች አውሮፕላን ኤይር  አልጄሪያ ተከስክሶ 102 ሰዎች ከሞቱ ወዲህ አልጄሪያ አሰቃቂ የአውሮፕላን አደጋ ሲገጥማት ይህ የመጀመሪያው ነው።

በአቬዬሽን አደጋ ከ 2014 ወዲህም ከፍተኛው እንደሆነም ታውቋል።

ንብረትነቱ የማሌዢያ አየር መንገድ የሆነ  አውሮፕላን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በሃምሌ 2014 ዩክሬን ውስጥ በመመታቱ  298 መንገደኞች እና የአውሮፕላኑ ሰራተኞች ማለቃቸው ይታወሳል።