የወረዳ አመራሮችን ለማስለቀቅ አባገዳዎች ሽምግልና መያዛቸው ተሰማ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 25/2011) በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ታጣቂዎች ያገቷቸውን ሶስት የወረዳ አመራሮችን ለማስለቀቅ አባገዳዎች ሽምግልና መያዛቸው ተገለጸ።

ባለፈው ዓርብ ከስብሰባ ሲመለሱ መንገድ ላይ ታፍነው የተወሰዱት የገላና ወረዳ አመራሮች የት እንደሚገኙ የታወቀ ነገር የለም።

ፋይል

ታፍነው ከተወሰዱት አንዱ የወረዳው የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ እንደሆኑ ታውቋል።

በሌላ በኩል ከሞያሌ ሲመለስ በነበረ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ተኩስ መከፈቱን ተከትሎ በተወሰደ ርምጃ 10 ሰዎች በተገደሉባት ፊንጭ ውሃ ከተማ ውጥረት መንገሱን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከመከላከያ አንድ ወታደር መገደሉም ታውቋል።

ምዕራብ ጉጂ ዞን በዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ግጭትና በኦነግ ታጣቂዎች ጥቃት ያለፉትን ሁለት ሳምንታት በውጥረት ቆይቷል።

ለከርሞውም ሰላም ስለመምጣቱ እርግጠኛ መሆን አልተቻለም። ባለፈው ዓርብ በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የተፈጠረውን አለመረጋጋት በተመለከተ ስብሰባ ውለው ሲመለሱ የነበሩ የገላን ወረዳ ሶስት አመራሮች በኦነግ ታጣቂዎች ታፍነው ተወሰዱ።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የገላን ወረዳ አንድ አመራር ለኢሳት እንደገለጹት የጸጥታና አስተዳደር ዘርፍ ሃላፊ አቶ ዳንዔል ቁጢን ጨምሮ ሶስት የምዕራብ ጉጂ ገላና ወረዳ ባለስልጣናት በኦነግ ታጣቂዎች ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ የት እንዳሉ ሳይታወቅ አንድ ሳምንት ሊሆናቸው አንድ ቀን ቀርቷል።

በወለጋና በጉጂ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ኦዴፓን የበታች መዋቅር ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ ያለው ኦነግ በምዕራብ ጉጂ ገላና ወረዳ አፍኖ የወሰዳቸው አመራሮች የዚሁ እንቅስቃሴው አካል መሆኑን ነው ለማወቅ የተቻለው።

ይሁንና ለኢሳት ዛሬ በደረሰው መረጃ መሰረት አባገዳዎች ሽምግልና ተቀምጠዋል።

ጫካ ለጫካ በመሽሎክሎክ ጥቃት ከሚሰነዝሩት የኦነግ ታጣቂዎች ጋር መነጋገር የጀመሩት አባገዳዎቹ ጥሩ ዜና ይዘው እንደመጡም ዘግይቶ ከመጣው የገላን ወረዳ አንድ አመራር መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

ምናልባትም በነገው ዕለት የታገቱት ሶስቱ አመራሮች ሊለቀቁ እንደሚችሉ ነው አባገዳዎቹ ለገላን ወረዳ አስተዳደር ያስታወቁት።

በአባገዳዎቹና በኦነግ ታጣቂዎች መካከል ምን ዓይነት ስምምነት ተደርሶ አመራሮቹ እንደሚለቀቁ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት ያደርግነው ጥረት አልተሳካም።

የኦነግ ታጣቂዎች ከወለጋ ቀጥሎ በብዛት የሚንቀሳቀሱበት አካባቢ እንደሆነ በሚገለጸው የምዕራብ ጉጂ ዞን በተለይም ከአባያ እስከ ገላና ባሉ አካባቢዎች እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።

የኢሳት ምንጮች እንደሚሉት የኦነግ ታጣቂዎች በምዕራብ ጉጂ ዞን ለዶ እና ሰርቲ በሚባሉ አካባቢዎች ሰፍረዋል።

መከላከያ ሰራዊት ሲመጣባቸው ጊዜያዊ ካምፓቸውን እያፈረሱ ወደ ጫካ እንደሚሸሹ ነው የአካባቢው ነዋሪዎች የሚገልጹት።

የጥቃት ዒላማቸው የመንግስት መዋቅርና የመንግስት የገንዘብ ተቋማት ናቸው ተብሏል።

በቅርቡ ከሻኪሶ የተጫነ ከ6 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ገንዘብ ለመዝረፍ ያደርጉት ጥረት መጨናገፉን መዘገባችን ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከትላንት በስትያ ከሞያሌ በመመለስ ላይ በነበረ የመከላከያ ሰራዊት ላይ በምዕራብ ጉጂ ዞን ፊንጭ ውሃ ከተማ ላይ ተኩስ መከፈቱን ተከትሎ 10 ሰዎች መገደላቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ከመከላከያ ሰራዊቱም አንድ ወታደር በግጭቱ መገደሉ ታውቋል።

ዘግይቶ በደረሰን ዜናም ትላንት ምሽት በምዕራብ ጉጂ ዞን ቶሬ ከተማ የኦነግን ታጣቂዎች በማሰስ ላይ ያለ የመከላከያ ሰራዊት በስህተት አንድ አርሶ አደር መግደሉ ተመልክቷል።

አካባቢው አሁንም ውጥረት ነግሶበት እንዳለም ከምንጮች መረጃ ለማወቅ ተችሏል።