በሞያሌ የሰዓት እላፊ ተደነገገ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 25/2011)በሞያሌ ከተማ ከትላንት ጀምሮ የሰዓት እላፊ መደንገጉ ተገለጸ።

የሞያሌ ከተማ ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስት የጣለው የሰዓት እላፊ ገደብ በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች ጥያቄ መሰረት የተፈጸመ መሆኑንም አስታውቋል።

ላለፉት ሁለት ሳምንታት እንደአዲስ ባገረሸው ግጭት ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ የተጣለው የሰዓት እላፊ ገደብ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 3 ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት ድረስ ማንኛውንም ዓይነት እንቅስቃሴን ይከለክላል።

በሞያሌና በዙሪያዋ በሚገኙ አካባቢዎች ባለፈው አንድ ዓመት በዘለቀው ግጭት ከ10ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለው ወደ ጎረቤት ሀገር ኬኒያ መሰደዳቸው የሚታወቅ ነው።

በገሪና በቦረናዎች መካከል ሞያሌን ማዕከል አድርጎ የጀመረው ግጭት መብረድ ሳይችል አንድ ዓመቱን ተሻገር።

ለወትሮው አልፎ አልፎ ይከሰት የነበረውና የመሬት ይገባኛል ጥያቄን መነሻ ያደረገው ግጭት በኢትዮጵያ የተከሰተውን ለውጥ ተከትሎ ወደ ከፋ ደም አፋሳሽ ውጊያ ተቀይሯል።

በአንድ ዓመት ብቻ ከሁለት መቶ በላይ ንጹሃን ያለቁበት ግጭት ተከስቷል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ባለፉት ሁለት ሳምንት ግጭት ይበልጥ አገርሽቶ የ40 ሰዎችን ህይወት አጥፍቷል። ሁለቱም ወገኖች አንዳቸው አንዳቸውን በጠብ ጫሪነት ይከሳሉ።

በክልል ደረጃ የሚገኙት የኦሮሚያና የሶማሌ ክልል ባለስልጣናት ግጭቱን ለመፍታት  በሙሉ ፍቃደኝነት እየሰሩ መሆናቸው ቢገለጽም በቦረና ዳዋ የሚገኙ የዞንና የወረዳ አመራሮች በተቃራኒው መቆማቸውን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።

ኢሳት ያነጋገራቸው የሶማሌ ክልል የጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዲ አዲል ችግሩ ከክልላቸው መንግስት አቅም በላይ በመሆኑ የፌደራል መንግስቱ ጣልቃ እንዲገባ መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትም የሞያሌውን ቀውስ ለማርገብ የፌደራል መንግስቱ አከባቢውን እንዲቆጣጠር ጥሪ ማድረጉ ነው የተገለጸው።

በጊዜያዊነት የተሰየመው የሞያሌ ከተማ ኮማንድ ፖስት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ከተማዋንና ዙሪያዋን የተመለከተ የጸጥታና ደህንነት ስራውን ከሁለቱም ወገኖች ተረክቦ ሰላም የማስፈን ርምጃ መውሰድ ጀምሯል።

ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስት ባለፈው ማክሰኞ ለኦሮሚያው ቦረና ዞንና ለሶማሌ ክልሉ ዳዋ ዞን አስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች በላከው ደብዳቤ በሞያሌ ከተማ የሰዓት እላፊ መደንገጉን አስታውቋል።

በደብዳቤው ላይ እንደተመለከተው ሁለቱ ክልሎች በጠየቁት መሰረት የፌደራል መንግስቱ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ለፌደራል ፖሊስና ለጸረ ሽብር ግብረ ሃይል ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

ትዕዛዙን ተከትሎ በጊዜያዊነት የተቋቋመው የሞያሌ ከተማ ኮማንድ ፖስት ሰላምና ደህንነቱን ለማረጋገጥ የሚረዳ ላልተወሰነ ጊዜ የሚቆይ የሰዓት ዕላፊ ገደብ መቀመጡን አስታውቋል።

በዚህም መሰረት ከትላንት የሚጀምር የሰዓት ዕላፊ ገደብ በሞያሌ ከተማ ተግባራዊ ሆኗል።

ማታ ከምሽቱ ሶስት ሰዓት እስከንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ መጠጥ ቤቶችንና መደብሮችን ጨምሮ ማንኛውም ዓይነት የንግድ እንቅስቃሴ ገደብ ተጥሎበታል።

በተመሳሳይ ከምሽት 3ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት መተርና ባጃጅን ጨምሮ ማንኛውም የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ በከተማዋ ተከልክሏል።

ከአምቡላንስ ውጪ በተጠቀሰው ሰዓት ማንኛውም ተሽከርካሪ መንቀሳቀስ አይችልም ብሏል ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስቱ።

ከመከላከያ ሰራዊት፣ ከፌደራል ፖሊስና ከጸረ ሽብር ግብረ ሃይል አባል ውጪ በተጠቀሰው ሰዓት በመንገድ ላይ የሚታይ ማንኛውም ሰው እንደተጠርጣሪ ተቆጥሮ በህግ የሚጠየቅና ርምጃ የሚወሰድበት መሆኑን በመጥቀስ ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስቱ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።