(ኢሳት ዲሲ–ጥር 22/2010)
የወልዲያ እግር ኳስ ክለብ ተበተነ።
የክለቡ ተጫዋቾች የተበተኑት በአካባቢው ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት መሆኑን ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
የወልዲያ ክለብ ተጫዋቾችና አሰልጣኙ ከተማዋን ለቀው ሄደዋል ተብሏል።
በሰሜን ወሎ የተለያዩ ከተሞች የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞ ተጠናክሮ ነው የቀጠለው።
የአካባቢውን ከተሞች በፍጥነት ያዳረሰው ተቃውሞ የሕይወትና የንብረት ጉዳት አስከትሏል።
ሕወሃት ከመሃል ሀገር ወደ ትግራይ ሸቀጦችንና ወታደራዊ ቁሶችን የሚያሻግርበት መንገድም አገዛዙን በሚቃወሙ የሰሜን ወሎ ነዋሪዎች ተዘግቷል።
ወልዲያ ከተማ ዳግም የተቃውሞው እምብርት ነች።
በወልዲያ ለ3 ቀናት የተጠራው ከቤት ያለመውጣት አድማ እንደቀጠለ ነው።
በከተማዋ ስፍር ቁጥር የሌለው ሰራዊት ቢሰፍርም የወልዲያ ነዋሪዎች ለአገዛዙ በትር አልተንበረከኩም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው እንግዲህ የወልዲያ እግር ኳስ ክለብ መበተኑ የተነገረው።
የወልዲያ እግር ኳስ ክለብ ከመቀሌ አቻው ጋር ከዚህ ቀደም በነበረው የጨዋታ ዝግጅት በደጋፊዎች በተፈጠረ አለመግባባት በከተማዋ የሰው ሕይወት መጥፋቱ ይታወሳል።
ከዚያም ወዲህ የሕወሃት አገዛዝ ጊዜውን ጠብቆ በፈጸመው የበቀል ጥቃት አንድ የ12 አመት ታዳጊን ጨምሮ 13 ሰዎች በወልዲያ ተገድለዋል።
እናም በዚህ ሁኔታ የወልዲያ እግር ኳስ ክለብ በጨዋታ መሳተፍ የሚችልበት ሁኔታ አልተፈጠረም።
የወልዲያ እግር ኳስ ክለብ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ገረመው ካሳ እንዳሉት ለተከታታይ ጨዋታዎች ዝግጅት ማድረግ ባለመቻሉ የክለቡ ተጫዋቾች እንዲበተኑ ተደርጓል።
ክለቡ በ12ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ከጅማ አባጅፋር ጋር ካደረገው ጨዋታ በኋላ በውድድር አልተሳተፈም።
እናም የክለቡ አመራሮችና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያስገባ ምቹ ሁኔታን እንዲፈጥሩ ስራ አስኪያጁ ጠይቀዋል።
ፌዴሬሽኑ በቀጣዮቹ ጥር 24ና 27 ክለቡ ያሉበትን ጨዋታዎች እንዲያሸጋግራቸው ስራ አስኪያጁ በደብዳቤ መጠየቃቸውንም የአማራ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል።