በመቄት ከተማ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 22/2010)

በሰሜን ወሎ መቄት ከተማ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ።

ከወልዲያ ወደ ደቡብ ጎንደር የሚወስደው መንገድም ተዘግቷል።

በጎንደር ዩኒቨርስቲ ተቃውሞ መነሳቱም ታውቋል።

በሰሜን ወሎ በተለያዩ አካባቢዎች ውጥረት መቀጠሉ ታውቋል።

መቄት ከወልዲያ ወደ ደቡብ ጎንደር በሚወስደው መንገድ ላይ ከሚገኙ ከተሞች አንዷ ናት።

በተለያዩ ጊዜያት በተነሱ ተቃውሞዎች መቄት ስሟ ሳይጠቀስ አያልፍም።

ሰሞኑንም ሰሜን ወሎን ካዳረሰው ተቃውሞ ጋር ተነስታለች።

የመቄት ነዋሪዎች የወልዲያውን ጭፍጨፋ ፣ በመርሳና ቆቦ የተፈጸሙትን የአጋዚ ሰራዊት የግድያ ርምጃዎች በመኮነን ዛሬ ለተቃውሞ አደባባይ መውጣታቸውን ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቷል።

የህወሀት አገዛዝን እንዲያበቃ በመጠየቅ በተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ከአገዛዙ ታጣቂዎች ጋር ግጭት ተፈጥሮ በርካታ ሰዎች መጎዳታቸው ታውቋል።

በዚህም መንገድ ተዘግቷል። ከሰሜን ወሎ ወደ ደቡብ ጎንደር የሚያመሩ ተሽከርካሪዎች ለሰዓታት ቆመው እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል።

በወልዲያ ዛሬ ውጥረት ነግሶ የዋለ ሲሆን ዛሬም ከተማዋ ሙሉ በሙሉ ከእንቅስቃሴ ውጭ ሆና መዋሏን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የፈተና መርሃ ግብር መቋረጡን ያመለከቱት የኢሳት ምንጮች መምህራን ከመኖሪያ ቤታቸው ወደ ዩኒቨርስቲው ለመጓጓዝ እንዳልቻሉም ገልጸዋል።

በመርሳና በሲሪንቃ ከሰሞኑ አንጻር ሁኔታዎች የረገቡ ቢመስሉም ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴ መመለስ እንዳልቻሉ ይነገራል።

በቆቦ ለሁለተኛ ጊዜ ህዝቡን ለማነጋገር የሄዱት አቶ ዓለምነህ መኮንን ከፍተኛ ተቃውሞ እንደገጠማቸው ለማወቅ ተችሏል።

ህዝቡ ለአቶ አለምነው ‘’ባንዳ ነህ፡ ለወያኔ ያደርክ ነህ’’ የሚሉ መልዕክቶችን በአዳራሹ ካሰማ በኋላ ስብሰባውን ረግጦ መውጣቱን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በሌላ በኩል በጎንደር ዩኒቨርስቲ ግጭት ተፈጥሮ በርካታ ተማሪዎች መጎዳታቸው ታውቋል።

ዛሬ በዩኒቨርስቲው ይጀመራል ተብሎ የታቀደው የፈተና መርሃ ግብር በተቃውሞ ምክንያት ሳይካሄድ መቅረቱን የገለጹት የኢሳት ምንጮች መነሻውም በወልዲያና መርሳ የተፈጸመው ጭፍጨፋ እረፍት ስለነሳን ፈተና አንቀመጥም የሚለው የተማሪዎች አቋም እንደሆነ ተጠቅሷል።

በአቅራቢያው የነበረው የአጋዚ ሃይል ወደ ዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ በመግባት ተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ድብደባ መፈጸሙን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በርካታ ተማሪዎች ተጎድተው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።

ከዩኒቨርስቲው ውጭ የአጋዚ ሰራዊት ህዝቡ ላይ ድብደባ መፈጸሙን የአይን እማኞች ገልጸዋል።

ዘግይተው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም የአጋዚ ሃይል ተማሪ ከግቢ እንዳይወጣ ዙሪያውን ከቦ ይገኛል።

በተያያዘ ዜና ትላንት ምሽት በጎንደር አይራ በሚባለው አካባቢ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ካምፕ ላይ ጥቃት መፈጸሙ ታውቋል።

ያልታወቁ ሃይሎች በፈጸሙት በዚሁ ጥቃት የተገደሉ የፖሊስ አባላት እንዳሉም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።