የወልቃይት የአማራ ማንነት ይከበርልን በማለት ጥያቄ ያነሱ ተወላጆች በጎንደር ስብሰባ አካሄዱ

የካቲት ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የጥያቄ አቅራቢዎች ተወካይ ባደረጉት ንግግር፣ የወልቃይት ህዝብ ላለፉት 24 አመታት ሳይፈልግ ማንነቱን ተነጥቋል ብለዋል። ያለፈቃዳቸው ወደ ትግራይ ክልል መዛወራቸውን ሲቃወሙ የነበሩ ሰዎች፣ ሌሊት እየተወሰዱ በመገደላቸው፣ የወልቃይት ሴቶች ባል አልባ ሆነዋል ሲሉ ተናግረዋል።
የትግራይ ክልል መሬታችንን፣ ሃብታችንን ዘርፏል፣ ህዝባችንንም አዋርዷል ያሉት ተወካዩ፣ በትግራይ ክልል እስር ቤት የታሰሩት አብዛኞቹ የወልቃይት ሰዎች ናቸው ብለዋል። የወልቃይት ህዝብ መጥፎ ሲባል ከነበረው ደርግ በባሰ ስርዓት እየተዳደረ መሆኑንም ተወካዩ ገልጸዋል።
ጥያቄያችን አዲስ ሳይሆን የነበረው ማንነታችን የመለስልን የሚል መሆኑንም ተናግረዋል ። በሌላ በኩል የትግራይና የአማራ ክልል ሽምግሌዎች ተመርጠው በወልቃይት ዙሪያ እየተነጋገሩ ነው ሲሉ የክልሉ ም/ል ፕሬዚዳንት አቶ አለምነው መኮንን ተናግረዋል።
የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አባይ ወልዱ የወልቃይት የማንነት ጥያቄ መልስ ያገኘ በመሆኑ፣ ልንደራደር አንፈልግም ሲሉ መግለጫ መስጠታቸው ይታወቃል።የትግራይ ተወላጆችም በሁመራ እና በተለያዩ ቦታዎች ሰልፎችን እያካሄዱ ፣ በጥያቄ አቅራቢዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ሲጠይቁ ሰንብተዋል።
በዛሬው የጎንደር ስብሰባ፣ ህዝቡ በክልሉ ውስጥ ተመሳሳይ ስብሰባዎች እንዲካሄዱ ወስኗል።