(ኢሳት ዜና–ሕዳር 11/2010) በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ የቀረቡት የወልቃይት አማራ የማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባላት በግራ ዳኛው መዳኘት አንፈልግም ሲሉ ተቃውሞአቸውን አሰሙ።
ሌሎች በችሎቱ የነበሩ ተከሳሾችም የመንግስትን አቋሚ በሚያንጸባርቁትና የሕወሃት የፖለቲካ አራማጅ በሆኑት ዘርአይ ወልደሰንበት አንዳኝም በማለት ድምጻቸውን አሰምተዋል።
የህግ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ ከተከሳሾቹ የተነሳው ጥያቄ ትክክል መሆኑንና እንደዚህ አይነት አቋም ያለው ዳኛ ተከሳሾቹ ቅሬታ ከማቅረባቸው በፊት ራሱ ነበር ይህን ጉዳይ መዳኘት አልችልም ማለት ያለበት።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት የዛሬ የፍርድ ቤት ውሎው ሰላማዊ አልነበርም ይላሉ በችሎቱ ላይ የተገኙት ታዛቢዎች።
በተለይ የችሎቱ የግራ ዳኛ ዘርአይ ወልደሰንበት ተከሳሾችን የመዳኘት አቅምም ሆነ መብት የላቸውም በሚል የተነሳው ተቃውሞ ፍርድ ቤቱን ያንቀሳቀሰና የበርካቶችን ድምጽ ያሰማ ሆኗል።
ጉዳዩ እንደዚህ ነበር ይላሉ ታዛቢዎቹ የወልቃይት አማራ የማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባላት አቶ አታላይ ዛፌን በማስቀደም ተቃውሞ አሰምተዋል።
የተቃውሞአቸው ዋነኛ መነሻም በግራ በኩል የተሰየሙትና ዘርአይ ወልደሰንበት የሚባሉት ዳኛ በማህበራዊ ድረገጾችና በቴሌቪዥን ጭምር በመቅረብ ወልቃይት የትግራይ ነው የሚል አቋማቸውን የሚያንጸባርቁ ግለሰብ ናቸው።
ይህንን አቋማቸን ይዘው ደግሞ እኛን ሊዳኙን አይገባም የወልቃይት አማራ የማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባላት ጥያቄ ነው።
በአባላቱ የተነሳው ጥያቄ ደግሞ በግንቦት 7ና ኦነግ ክስ የቀረበባቸውና በአጠቃላይ በችሎቱ የነበሩ ተከሳሾች ጥያቄው የወልቃይቶች ብቻ ሳይሆን የኛም ጭምር ነው ስለዚህ በኚህ ዳኛ ጉዳያችን ሊታይ አይግባል በሚል ድምጻቸውን አሰምተዋል።
አቶ አታላይ ዛፌ ቅሬታቸውን ሲያሰሙ እሱ ዳኛ፣ እሱ ተከራካሪ፣እሱ መልዕክት አስተላላፊ ሆኖ እንዴት ትክክለኛ ፍትህ ሊገኝ ይችላል ብለዋል።
ሁለተኛ ተከሳሽ ዘመነ ጌቴ በበኩሉ ማዕከላዊ የተደበደብኩት ወልቃይት የማነው እየተባልኩ ነው ታዲያ በዚህ ችሎት እኚህ ዳኛ ባሉበት እንዴት ፍትህን ላስብ እችላለሁ ሲል ተደምጧል።
የግራ ዳኛው ዘርአይ ከተከሳሾቹ የተነሳውን ቅሬታ ወደጎን በማለት የተከሰሳችሁት በወልቃይት አማራ ማንነት ነው ወይስ በሽብርተኝነት የሚለው የሚታይ ይሆናል ሲሉ ከተከሳሾቹ ቅሬታ ጋር ምንም የማይገናኝ ምላሽ ሰጥተዋል።
ቅሬታዎቹን ሲያስተናግድ የዋለው ችሎትም ተከሳሾች ዳኛው ይነሱልን የሚለውን ቅሬታቸውን በጽሑፍ እንዲያቀርቡ ለሕዳር 14፣15ና 18 ቀነ ቀጠሮ ተይዞላቸዋል።
የህግ ባለሙያው ዶክተር ሰማህኝ እንደሚሉት ከሆነ ከተከሳሾቹ የተነሳው ቅሬታ ትክክልና በህግ አግባብነት ያለው ነው።
ቅሬታ የቀረበበት ዳኛም ቢሆን በተለያዩ ድረ ገጾች ስለጉዳዩ እንደሚጽፍና እንደሚከታተል እየታወቀ ቅሬታ ሳይቀርብበት በፊት ራሱ ይህን ጉዳይ በግሌ ስለምከታተለው የዳኝነቱን ጉዳይ ማየት አልችልም ማለት ነበረበት ብለዋል።
የኦሮሞ ዲሞክራሲያ ግንባር አመራር አባል አቶ ሌንጮ ባቲ ደግሞ ዛሬ የተነሳው ጥያቄ የሁለትና የሶስት ሰዎች ጉዳይ ብቻ አይደለም ያላሉ።–ለ26 አመታት የኢትዮጵያ ህዝብ ሲመኘው ሲጠይቀው የቆየው የፍትህ ስርአት እንጂ
ይህ በእንዲህ እንዳለ በእስር ቤት ያለምንም ፍትሕ 5 አመታትን ሊደፍኑ ወራቶች የቀሯቸው የቀድሞ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታ የፍትህ ያለ እያሉ መሆናቸው ተሰምቷል።
ሪፖርተር በዘገባው እንዳወጣው ከሆነ የፍትህ ፍንጭን የማየት ተስፋ እንደሌላቸውና ለሳቸው በአሁኑ ሰአት የሚመኙት ነገር የተፋጠነ ውሳኔን ነው ብሏል።