የወልቂጤ አካባቢ ወጣቶች በልዩ ሃይል እየታፈሱ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 24/2011) በጉራጌ ዞን የወልቂጤ አካባቢ ወጣቶች በአካባቢው ልዩ ሃይል እየታፈሱ መሆኑ ተሰማ።

በጉራጌና በቀቤና ብሔረሰቦች መካከል ቀደም ሲል ተቀስቅሶ የነበረው ግጭትም አሳሳቢ ወደሚባል ደረጃ እየተሸጋገረ መሆኑን ኢሳት ወደ አካባቢው ደውሎ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ፋይል

በፌደራል ደረጃ ጉዳዩን ለመፍታት የተደረገው ሙከራ ሊሳካ አልቻለም የሚሉት የኢሳት ምንጮች ግጭቱ እንዲባባስ የሚፈልጉ አካላት ደግሞ በአካባቢው ውጥረት እየፈጠሩ ነው ብለዋል።

ሁኔታውን ለማረጋጋት የፌደራሉ መከላከያ ሃይል በአካባቢው መሰማራቱም ታውቋል።

በጉራጌና በቀቤና  ማህበረሰብ በኩል የተፈጠረው ችግር የአሁን አይደለም ትንሽ ቆየት ያለ ነው ይላሉ ወደ አካባቢው ደውለን ያነጋገርናቸው የአካባቢው ነዋሪዎች።–የችግሩ መንስኤንም አናውቅም በማለት።

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት በአካባቢው የሚነሱ በርካታ ጥያቄዎች ይኖራሉ።ነገር ግን እነዚህን ጥያቄዎች ለማስፈጸም የሚኬድበት ርቀት ግን ሃይል የተቀላቀለበት ነው ባይ ናቸው።

ይህንን ጉዳይ እንዲያስፈጽሙ በአካባቢው የተሰማሩ አካላት መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ አካባቢው መተው ከነዋሪዎች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅ ነገሮች ተሻሽለው ነበር ይላሉ ነዋሪዎቹ

እነሱ እንደሚሉት ነገሮች አቅጣጫቸውን እንዲስቱና ሁኔታዎች እንዲባባሱ ስራዎችን እየሰሩ ያሉ አካላት አሉ።

ነገሮችን ለማርገብ በተደረጉት ውይይቶች መኖራቸውንና ያንን ተከትሎም የአካባቢው ወጣቱ ነገሮችን በተባለው መንገድ እንዲፈቱ ተስማምቶ ወደ ቤቱ መመለሱ ታውቋል።

ይህ ባለበት ሁኔታና ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት ወጣቶችንም ማፈስ ተጀምሯል ይላሉ የኢሳት ምንጮች።

ነገሮችን ለማርገብ ወደ አካባቢው የመከላከያ ሃይል መሰማራቱንም ምንጮች ይገልጻሉ።

ከዚህም በላይ ነገሮቹን ከበድ ያደረገው ነገርም ተፈጥሯል ይላሉ።የሃገር ሽማግሌዎች ይፈቱታል የተባለው ችግር ወጣቶችን ወደ ማሳፈስ መሄዱ።

እንደ ምንጮቹ ከሆነ አሁን ወጣቶቹ ተረጋግተውና ነገሮች ወደ ግጭት እንዳያመሩ በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

ኢሳትም ነገሮቹ ይመለከታቸዋል፣በጉዳዩ ውስጥ አሉበት ወደ ተባሉት ሰዎች ደውሎ በነሱ በኩል ያለውን መረጃ ለማጣራት ያደረገው ጥረት ሳይሳካለት ቀርቷል።

እስከመጨረሻውም ተከታትሎ በነሱ በኩል ያለውን መረጃ ለማግኘት ጥረት እያደረገ ነው።