በአሶሳ ዩኒቨርስቲ ባሉት ተማሪዎች ትምህርት ተጀመረ

(ኢሳት ዲሲ–ሕዳር 24/2011) በአሶሳ ዩኒቨርስቲ ተቋርጦ የነበረው የመማር ማስተማር ሒደት ባሉት ተማሪዎች መጀመሩ ታወቀ።

ኢሳት ወደ ዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ደውሎ እንዳገኘው መረጃ ከሆነ በግቢው ውስጥ አብዛኛው ተማሪ ባይኖርም ያሉትን ተማሪዎች አሰባስቦ ለማስተማር እየተሞከረ ነው።

ተማሪዎቹ እንደሚሉት ከሆነ በግቢው ውስጥ ብዙ ተማሪ ካለመኖሩ የተነሳ ሁለት ክፍሎችን በአንድ ላይ አጥፎ ነው ትምህርቱ እንዲሰጥ እየተደረገ ያለው።

እንደነሱ አባባል ከሆነም ዩኒቨርስቲው ትምህርቱን ሲጀምር ምናልባትም ግቢውን ለቀው የሔዱት ተማሪዎች ይመለሳሉ በሚል ተስፋ ነው።

በግቢው ውስጥ ያለው ሁኔታ ግን አሁንም ደስ የማይልና አለመረጋጋት የሚታይበት መሆኑን ግን ኢሳት ያነጋገራቸው የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ሳይገልጹ አላለፉም።